ቀጥታ፡

በባለሀብቶች አድናቆት የተቸረው የኢትዮጵያ ባለልዩ ጣዕም ቡና

ቡሌ ሆራ፤ ታህሳስ 8/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ባለልዩ ጣዕም ቡና ዝግጅትና ልማት ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች አደነቁ።

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ የልዩ ጣዕም ቡና ዝግጅትና ልማት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሀብቶች ተጎብኝቷል፡፡

የኢትዮጵያን ቡና ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡ የዩርዳኖስ ባለሀብቶች መካከል አንዱ የሆኑት ሚስተር መሐሙድ አባውደን፤ የኢትዮጵያ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በጥራቱና በጣዕሙ ከሌላው ዓለም መለየቱ በገበያ ተፈላጊ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

የተፈላጊነቱ መጨመርም ብዛት ያለው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ከማስገኘት አልፎ አምራቹንና ባለሀብቱን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡

ባለልዩ ጣዕም ቡናን ለጃፓን፣ ለአሜሪካ፣ ለኮሪያና ለሌሎችም የዓለም አቀፍ ገበያዎች በማቅረብ ላይ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

የዚሁ አገር ባለሀብት ሚስተር አብደላ ሀኒያ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ባለልዩ ጣዕም ቡና ዝግጅትና ልማት ልምድና ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

''የምርቱ የተፈጥሮ ጣዕምና ጥራት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ውጤታማ አድርጎናል'' ያሉት ባለሀብቱ ''የምርት አቅርቦቱ የበለጠ እንዲሰፋ እንፈልጋለን'' ብለዋል፡፡

የሳራ ቡና ላኪና አቅራቢ ኩባንያ ባለቤት አቶ ሰኢድ ዳምጠውም "ባለ ልዩ ጣዕም ቡና በዓለም ላይ በቀዳሚነት የሚፈለግ ምርት ነው" ብለዋል፡፡

ከውጭ አገር ባለሀብቶችና ኩባንያዎች ጋር በመተባበር ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለገበያ በማቅረብ ምርቱን እያስተዋወቁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት ለባለሀብቱ እያደረገ ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍም ለበለጠ ስራ ማነሳሳቱን በመጠቆም፡፡

ዘንድሮ ባለ ልዩ ጣዕም ቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ካቀዱት 10 ሺህ ቶን ውስጥ እስካሁን 2 ሺህ 500 ቶን መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዱላ ሂርባዬ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ከዞኑ ከፍተኛ የቡና ምርት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

በዞኑ የሚገኙ ከ200 በላይ የደረቅና የእሸት ቡና ኢንዱስትሪዎች በባለ ልዩ ጣዕም ቡና ምርት አቅርቦት ዝግጅት ስራ ላይ እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ከዞኑ ለመሰብሰብ ከታቀደው ውስጥ 113 ሺህ ቶን ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ገበያዎች የማቅረብ እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

የጉጂን የተፈጥሮ ቡና ጣዕምና ጥራት ለውጭ አገር ተጠቃሚዎች ኩባንያዎችና ባለሀብቶች እያስተዋወቁ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በተሻሻለ የቡና ዝርያ አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ምርታማነቱን የማሳደግ ስራም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም