ቀጥታ፡

በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ የሚስተዋሉ ሙስናና እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ  ሙስናንና እና ብልሹ አሰራሮችን  ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየተገነባ መሆኑን  የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ፡፡

"ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋማዊ ተልዕኮ ስኬት" በሚል መሪ ሃሳብ ዘርፍ ተኮር የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ስልጠና ለከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች እየተሰጠ ነው፡፡


 

የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፈቃዱ ሰቦቃ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሥነ ምግባራዊ አመራርነት ለተቋም ተልዕኮ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመታገል የአመራሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

አመራሩ ራሱን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር በማራቅ ከመንግስትና ከህዝብ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የከተሞች እድገት ከመሠረቱ በትክክለኛና በጠንካራ ህግ ከተመራ ፈጣን ሀገራዊ እድገት ለማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ይህ ካልሆነ ግን ህገ ወጥ ሠፈራ፣ መሬት ወረራ፣ ኢ-ፍትሃዊ አሠራርና የጥቂቶች ተጠቃሚነት ይስፋፋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አመራሮችና ባለሙያዎች ሙስናንና እና ብልሹ አሰራርን  ለመከላከል የሚያስችላቸውን አቅም ለመገንባት የተጀመረው ስራ በትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ነገዎ በበኩላቸው፤ በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ የሚስተዋለውን ሙስና በተጨባጭ መዋጋት የሁሉም ኃላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ሀብትን በፍትሃዊነት ለመጠቀም፣ ፍትሃዊ ውድድርን ለማስፈን እና ቀጣይነት ያለው የከተሞች ዕድገትን ለማምጣት ሙስናን መከላከል  የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ሙስና ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግር በማስከተልና ፍትሃዊነትን በማዛባት የሀገርን ዘላቂ ልማት የሚያቀጭጭ እና የሁሉም ዘርፎች ትልቅ ፈተና መሆኑን አመላክተዋል።

በከተማ እና መሠረተ ልማት ዘርፍ ያለውን ሙስና የከፋ የሚያደርገው ለህብረተሰብ ልማት በሚውሉ መሬት እና መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸም መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ከተሞች የብልሹ አሠራርና የሙስና ወንጀል ሥጋት እንዳይሆኑ በስነ ምግባር ልዕልናው የበቃ አመራርና አገልጋይ ለመፍጠር የሚያስችል ተከታታይ የስብዕና ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም