ቀጥታ፡

የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ተቀባይነት ተጠቅመው ለሰላም መረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል- አቶ መሃመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 8/2017(ኢዜአ)፦ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን በዜጎች ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትር መሃመድ እድሪስ አሳሰቡ።

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ጋር በመሆን ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫና የውይይት መድረክ አካሄዷል።


 

በውይይቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር መሃመድ እድሪስን ጨምሮ ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ኃላፊዎች እና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ሥራ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል።

አቶ መሐመድ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ ያላቸው ተደራሽነት ሰፊ በመሆኑ ሰላምን ለመገንባት ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።

መገናኛ ብዝሃኑ በማህበረሰቡ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም ግጭቶች እንዳይከሰቱ እና ከተከሰቱም በኋላ እንዳይባባሱ የበኩላቸው ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ተቋማቱ ያላቸውን የቅንጅት አሰራር ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።


 

የሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ እምቅ ማህበረ-ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም ሀገራዊ ሰላምን ማረጋገጥ ላይ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሚዲያ ክትትልና አቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ ባለስልጣኑ ከሚኒስቴሩ ጋር በሰላም ግንባታ ሂደት በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም