የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አሻራ ያረፈበት የኢትዮ-ታንዛንያ ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አሻራ ያረፈበት የኢትዮ-ታንዛንያ ወዳጅነት

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የታንዛንያ የውጭ ጉዳይ እና ምሥራቅ አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ማሕሙድ ታቢት ኮምቦ በስብስባው ላይ ለመሳተፍ ትናንት አዲስ አበባ ገብተዋል። ስብስባው የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የሁለትዮሽ ትስስር እና የጋራ ትብብር የማጠናከር ዓላማ የያዘ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም ከታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከነበሩት ጃንዋሪ ማካምባ ጋር ባደረጉት የሁለትዮሽ ውይይት የኮሚሽኑን ስብስባ ለማካሄድ ከስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያና ታንዛንያ የሁለትዮሽ ወዳጅነት በቅርበት ለመረዳት የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄን ማየት ግድ ይላል።
የመላው ጥቁር ሕዝቦች ንቅናቄ የሆነው ፓን አፍሪካኒዝም ጅማሮ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት የሆነችው ኢትዮጵያ የንቅናቄው ፋና ወጊ በመሆን ወሳኝ ሚና ተጫውታለች።
የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር አብረው በመቆም ትግል ሲያደርጉ ከነበሩት አገራት መካከል ታንዛንያ ትገኝበታለች። በፓን አፍሪካኒዝም ትግል ውስጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ መሪዎች መካከል ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና የታንዛንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጁሊዬስ ኔሬሬ ተጠቃሽ ናቸው።
መሪዎቹ ለአፍሪካ አገራት ከቅኝ አገዛዝ መውጣት ትልቅ ሚና በመጫወት ሕያው አሻራቸውን አሳርፈዋል። የኢትዮጵያና ታንዛንያ የሁለትዮሽ ግንኙነት በእነዚህ መሪዎች ጊዜ የተጀመረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አገራቱ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጣር ግንቦት 25 ቀን 1963 የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (በአሁኑ መጠሪያው የአፍሪካ ኅብረት) መቋቋሙ ሲበሰር መስራች አባል አገራት ነበሩ። ኢትዮጵያና ታንዛንያ በየአገራቱ ኤምባሲያቸውን በይፋ በመክፈት የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናክር እየሰሩ ይገኛሉ።
አገራቱ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችላቸው በርካታ አቅሞች አሉ። ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ ባላቸው የቁም እንሥሳት ኃብት ከአፍሪካ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ አገራት ናቸው።
ሁለቱ አገራት በሚያደርጓቸው የጋራ ምክክሮች ይሄን ሰፊ ኃብት በመጠቀም የንግድ እና ኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ጊዜ ያነሳሉ።
ግብርና፣ የሰብል ምርት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እና አቪዬሽን ከሁለቱ አገራት የትብብር መስኮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳሉ። የኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚ በርካታ ታንዛንያውያን ፓይለቶች እና ኢንጂነሮችን አሰልጥኖ አስመርቋል። አቪዬሽንም የሁለቱ አገራት ቁልፍ የትብብር መስክ በሚል ይነሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በታንዛንያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሁሉ ሀሰን ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
አገራቱ በወቅቱ በባህልና ኪነ-ጥበብ፣ በግብርና እንዲሁም በኤሌክትሪክ ኃይል ንግድ ላይ በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቶቹ የሁለቱ አገራት ትብብር ይበልጥ ለማጠናክር ትልቅ ፋይዳ አላቸው።
የዛሬው የኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባም የስምምነቶችን አፈፃጸም በመገምገም ትግበራውን ማፋጠን የሚያስችል አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ከሰሞኑ የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት አካል የሆነው ከኬንያ ወደ ታንዛንያ የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመር የሙከራ የኃይል አቅርቦት መጀመሩ ይታወቃል። የቀጣናው ከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ (ሃይዌይ) ፕሮጀክት የመጀመሪያው የኃይል ትስስር ኢትዮጵያና ኬንያን ያስተሳሰረ መሆኑ ይታወሳል።
የፕሮጀክቱ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ ከኬንያ ወደ ታንዛኒያ የተዘረጋ ሲሆን የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ተጠናቆ የሙከራ ኃይል አቅርቦት መጀመሩን የውኃና ኢኒርጂ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ይህ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር በተመጣጣኝ ዋጋ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በማረጋገጥ በሀገራት መካካል ትብብርን እና የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
የኃይል አቅርቦት መጀመሩ ከኢትዮጵያ እና ታንዛንያ አልፎ በቀጣናው ያለውን ትስስር ለማፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል።
ሁለቱ አገራት በቅርቡ ወደ ትግብራ ምዕራፍ የገባው የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በአገራቸው ፓርላማ ማጽደቃቸው ይታወቃል።
ስምምነቱ በናይል ተፋስስ የውኃ ኃብትን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መልኩ በበጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ነው። አገራቱም በውኃ ኃብት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ያስተሳሰራቸው ኢትዮጵያ እና ታንዛንያ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ትብብራቸውን ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሸጋግር የሚያስችሉ ሰፊ እድሎች ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል።