ቀጥታ፡

ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠት የተበላሸ ከ406 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ ተጠገነ

ደሴ፤ታህሳስ 8/2017 (ኢዜአ)፦ በአካባቢው በአገልግሎት ብዛት የተበላሸ ከ406 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፋልት መንገድ በመጠገን ለአገልግሎት ማብቃቱን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ መንገድ አውታር ማኔጅመንት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የመንገድ አውታር አስተዳደር ቡድን መሪ ኢንጂነር ግዛቸው የሽዋስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ጽህፈት ቤቱ ምስራቅ አማራን እና አፋር ክልልን በከፊል 2 ሺህ 855 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ይከታተላል።

በአገልግሎት ሂደትና በድንገተኛ አደጋ ለብልሽት የተጋለጡ መንገዶችን  መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡


 

በተያዘው በጀት ዓመትም ለብልሽት የተዳረገ 1 ሺህ 72 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለመጠገን አቅዶ እየሰራ ነው።

በዚህም ባለፉት አምስት ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ406 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ መንገድ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ተጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ጥገና ከተደረገላችው መንገዶች መካከል ሰመራ-ዱብቲ፣ ሚሌ-ጋላፊ፣ ኮምቦልቻ-ባቲ፣ ኮምቦልቻ-ደሴ፣ ደሴ-ኩታበር፣ ኮምቦልቻ-መካነ ሰላም፣ ኮምቦልቻ-ከሚሴ-አጣዬና ሌሎችም ይገኙበታል።

በተጨማሪም በወልድያ ከተማ አስተዳደር የሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድ ግንባታ እየተሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በቀሪ ወራትም ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መንገዶች ጠግኖ ለመጨረስ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

መንገዱ ተጠግኖ ለአገልግሎት መብቃቱ በህብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ከማስቀረቱም በላይ የተሽከርካሪን ጉዳት የሚያስቀር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ከደሴ-ኮምቦልቻ-ባቲ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አሽከርካሪዎች መካከል አቶ ቃሲም በሽር እንዳሉት፤ የመንገዱ መበላሸት ተገልጋዮችን ከማሰቃየቱ ባለፈ በተሸከርካሪ ላይም ጉዳት ያደርስ እንነበር አስታውሰዋል፡፡

መንገዱ ለረጅም ጊዜ ሲያስቸግር እንደነበር አንስተው፤ ዘንድሮ ተጠግኖ ስራ በመጀመሩ ችግሩ እንዲቀረፍ አድርጓል ብለዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 196 ኪ.ሜ መንገድን በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ ጠግኖ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉም ተመላክቷል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም