ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህር ዛፍ ተክልን በመንቀል ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን ለማልማት የተጀመረው ጥረት ውጤት እየተገኘበት ነው

ዱራሜ ፤ታህሳስ 8/2017 (ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባህር  ዛፍ ተክልን በመንቀል ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን ለማልማት እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እየተገኘበት መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።

በክልሉ በከምባታ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ላዳ ቀበሌ ባህር ዛፍን በመንቀል በፍራፍሬ፣ ቡናና፣ቅመማ ቅመም ሰብሎች የለማ የአርሶ አደር ማሳ በክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት እየተጎበኘ ነው ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ካለው ማሳ በርካታው  በባህር ዛፍ የተሸፈነ ነው ።


 

የባህር ዛፍ ተክል የመሬት ለምነትን በመቀነስ ምርትና ምርታማነት ላይ እያሳደረ የሚገኘው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል  ባለመሆኑ ይህን ለመቀልበስ በተቀናጀ መልኩ  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር አሳታፊ በሆነ መልኩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም አቶ ኡስማን ተናግረዋል ።

እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ ከዚህ ውስጥ አንዱ በክልሉ ባህር ዛፍን በመንቀል ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎችን ማልማት ከተያዙ አቅጣጫዎች መካከል  ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥም አበረታች ውጤት መታየቱን ገልጸዋል ።

የባህር ዛፍ ተክል የራሱ የሆነ ኢኮሚያዊ ጥቅም ቢኖረውም አድጎ ጥቅም ላይ ለመዋል ረጅም ጊዜ ከመውሰዱ ባለፈ ውሃን በከፍተኛ መጠን የሚጠቀም በመሆኑ የእርሻ መሬት እርጥበትና ለምነትን በመጉዳት ምርታማነት እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።

ለአርሶ አደሮች  ግንዛቤ በመፍጠርና በመግባባት ባህር ዛፍን በመንቀል በምትኩ ለምግብነት በሚውሉ ሰብሎች ልማት ላይ እንዲሰማሩ የተጀመሩ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የምልከታው ዓላማ ተግባሩን ለማስቀጠልና ልምዱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት  መሆኑን አስረድተዋል ።

በከምባታ ዞን ቃጫ ቢራ ወረዳ ላዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መለሰ ግዴቦ በበኩላቸው እንዳሉት በባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት የባህር ዛፍ ተክል ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል።

የባህር ዛፍ ተክልን 7 ዓመት ጠብቀው እንደሚጠቀሙበትና በዚህም በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንደማያመጣ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ ባህር ዛፉን ሙሉ በሙሉ ለመንቀል መወሰናቸውን አስረድተዋል።

በዚህም የነበራቸውን ሁለት ሄክታር የባህር ዛፍ ማሳ በመንቀል ቡናና እንሰትን ጨምሮ በተለያዩ ለምግብነት በሚውሉ ሰብሎች ተክተው ማልማት ከጀመሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ጠቁመዋል  ።

አሁን ለምግብነትም ሆነ ለኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተሻለ ተስፋ ይዘናል ያሉት አቶ መለሰ "በግብርናው ዘርፍ በርትተን እንድንሰራ እየተሰጠ ያለው ግንዛቤና ድጋፍ ለውጦችን እንድናይ እያደረገን ነው" ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም