ቀጥታ፡

የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ አገራዊ ድሎችን ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ):- የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ አገራዊ ድሎችን ማሳካት እንደሚቻል ትልቅ ማሳያ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተርኪዬ አደራዳሪነት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የደረሱበትን የአንካራ ስምምነትን አስመልክቶ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አቶ አወል ኢትዮጵያ የባህር በር ሳይኖራት በኪራይ ወደብ ለረጅም ጊዜ ስትጠቀምበት መቆየቷንና የወደብ ጥያቄ ሳይመለስ መቆየቱን ገልጸዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም እና ሉዓላዊነት በማይጎዳ መንገድ የቀይ ባህር ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባት ያነሱት ጥያቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የዓለም አቀፍ ሕግ ድጋፍ ያለው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተፈራረሙት ስምምነት የባህር በር ጥያቄ እንዲመለስ በር ከፋች መሆኑ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የማንንም ሉዓላዊነት እና ጥቅም ሳይነካ በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ መንገድ የባህር በር የማግኘት እና የመጠቀም ፍላጎቷን ስታንጸባርቅ መቆየቷን አመልክተዋል።

የአንካራው ስምምነትም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይህን አገራዊ መሻት እውን ለማድረግ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም