ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር በኢኮኖሚ እና በንግዱ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት ትሰራለች - አምባሳደር ሙክታር መሀመድ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ጋር በኢኮኖሚ እና በንግዱ ዘርፍ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደምትሰራ በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሀመድ ገለጹ።

በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለአልጄሪያው የፌሞካ ቡና ንግድ ድርጅት የኢትዮጵያን ቡናን የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር አካሄዷል።

መርሃ ግብሩ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ ትስስር ማጠናከርን ያለመ ነው።

አምባሳደር ሙክታር መሀመድ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ ለረጅም ጊዜ የቆየውን ወዳጅነታቸው በኢኮኖሚ እና በንግድ መስኮች ማጠናከር ይኖርባቸዋል።

በዚህ ረገድ የፌሞካ ቡና ንግድ ድርጅት የጀመረው የኢትዮጵያን ቡና በአልጄሪያ የማስተዋወቅ ተግባር አድንቀዋል።

ቡና በኢትዮጵያ እና በአልጄሪያ ተወዳጅ መጠጥ መሆኑን አውስተው አቅራቢዎች የኢትዮጵያን ቡና ከሶስተኛ ወገን ከመግዛት ይልቅ በቀጥታ ቢገዙ ውጤታማ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

ኤምባሲው ለድርጅቱ ድጋፍ ለማድረግ እና የአገራቱን የንግድ ግንኙነት ለማሳለጥ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የፌሞካ ቡና ንግድ ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች ለኢትዮጵያ ቡና ያላቸውን አድናቆት ገልፀው የኢትዮጵያ ቡናን ከሶስተኛ ወገን ሳይሆን ከሀገሪቷ በቀጥታ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እና በአልጄሪያ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም መግለጻቸውን በአልጀርስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም