ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያዎች ተሞክሮ መውሰድ እንደምትሻ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን የትምህርት ዘርፍ ማሻሻያዎች ተሞክሮ መውሰድ እንደምትሻ ገለጸች
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 7/2017(ኢዜአ):- ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ እያደረገች ከምትገኘው ማሻሻያ ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግ አስታወቀች።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋብሬላ ቻንግሰን ቻንግ የተመራ ልዑክን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ዜጎች እየሰጠች ባለችው የትምህርት እድል ላይ ያተኮረ ነው።
የትምህርት ሚኒስትሩ ለልዑካን ቡድኑ መንግሥት ገቢራዊ እያደረጋቸው ያሉ የትምህርት ዘርፍ ሪፎርሞችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መውጫ ፈተናን እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የመግቢያ ፈተናን እየወሰዱ እንደሚገኝና ደቡብ ሱዳንም መሰል አሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደምትችል ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ዜጎች ባለፉት ዓመታት በርካታ የትምህርት እድል ሲሰጥ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
የደቡብ ሱዳን የከፍተኛ ትምህርት ሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋብሬላ ቻንግሰን በበኩላቸው ከሁለት ዓመት በፊት በአገራቱ መካከል የተፈረመው የትምህርት ዘርፍ የመግባቢያ ስምምነት በጥሩ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ዜጎች በተሰጠው የነፃ ትምህርት እድልና እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብን አመስግነዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ ጥራትና ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት እየሰራች ያለውን ሥራ አድንቀዋል።
በደቡብ ሱዳንም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጠንካራ እንዲሆን በማድረግ በኢትዮጵያ የትምህርት እድል የሚሰጣቸው ተማሪዎችም የተሻለ ውጤትና ብቃት ያላቸው ለማድረግ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።