ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ የሁለትዮሽ ስምምነት አተገባበር ላይ ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 7/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ የሁለትዮሽ ስምምነት አተገባበርን አስመልክተው ዛሬ ውይይት አካሂደዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ ከሳውዲ ዓረቢያ የሰው ኃይል አስተዳደር ተወካዮች ጋር ምክክር አድርገዋል።

ውይይቱ በውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዘርፍ በኢትዮጵያ እና በሳውዲ አረቢያ መካከል የተፈረመውን የሁለትዮሽ ስምምነት አተገባበርና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው የዜጎችን መብት ደህንነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን ዓላማው ባደረገው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አስመልክቶ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የስምሪቱ ሂደት ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ሥልጠና እና ምዘና ድረስ የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ ታግዞ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ሥራውን ይበልጥ ለማዘመንና ከብልሹ አሰራር በማጽዳት ብቁና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለሥራ ገበያው ለማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከሳውዲ ዓረቢያ የሰው ኃይል አስተዳደር ተወካዮች ጋር የተጀመረው ተቀራርቦ የመስራት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ የሰው ኃይል አስተዳደር ተወካዮች በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ አገራት ሥራ ስምሪት ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችን አድንቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም