አፍሪካን ለመምራት ተስፋ የሰነቁ የህጻናት ፓርላማ መሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካን ለመምራት ተስፋ የሰነቁ የህጻናት ፓርላማ መሪዎች
የኬንያ ህጻናት ፓርላማ መሪ የ17 አመቷ አግነስ ምወንድዋ የህጻናት ሰብዓዊ መብትን፣ የዴሞክራሲ ልምምድንና መሪነትን ለማዳበር የህጻናት ፓርላማ መሰረት እንደሆናት ተናግራለች።
ህጻናትን የሚመለከቱ ጉዳዮች የኬንያ ህጻናትን በመወከል በተለያዩ መድረኮች ድምጻቸውን በማሰማት እየሰራች እንደምትገኝ ልምዷን አጋርታለች።
መንግስት በሚያወጣቸው ህጎች ህጻናትን ታሳቢ እንዲደርጉ፣ የህጻናት መብት ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙ፣ የወጡ ህጎች እንዲተገበሩ ጫና እንደሚያደርጉም ጨምራለች።
ፓርላማው ከመጠናከሩ በፊት ህጻናት መብታቸውን በአግባቡ ተገንዝበው ከመጠየቅ አንጻር ክፍተት እንደነበር በማስታወስ በአሁኑ ወቅት መብታቸውን አውቀው መጠየቅ ጀምረዋል።
አግነስ ምወንድዋ በህጻናት ፓርላማ የጀመረችውን መሪነትና ተጽእኖ ፈጣሪነት በአፍሪካ የዳበረ ፍትህ፣ እኩልነት እና አንድነት እንዲመጣ ወጣት መሪ የመሆን ህልምን አሳድሮባታል።
የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ የአዲስ አበባ ተወካይ ኢክራም ሲራጅ የህጻናት ፓርላማ የዴሞክራሲና የአመራር ልምምድን ለማሳደግ እያገዛቸው እንደሆነ ተናግራለች።
የአፍሪካ ሀገራት የህጻናት ፓርላማ ትብብርንና አንድነትን በማጠናከር የወጣት መሪዎች መፈጠሪያ ማድረግ እንደሚቻል አንስታለች።
የኡጋንዳ ህጻናት ተወካይ ሻኒታ ናሳኛ በበኩሏ አፍሪካ ለሚያስፈልጋት ወጣት መሪ ለዛሬ ህጻናት በነጻነት የሚናገሩበትን እድል ማመቻቸት መሰረት እንደሆነ አንስታለች።
በዓለም ላይ የሚገኙ ህጻናት ስለራሳቸው ጉዳይ በቀጥታ፣ በድፍረትና በአንድነት በመናገር ፍትሃዊ መሪ የመሆን ልምምድን መጀመር ይኖርባቸዋል ብለዋል ህጻናቱ።
በአፍሪካ አጀንዳ 2063 አንድነቷ የተጠናከረ፣ ሰላም የሰፈነባትና በፓን አፍሪካኒዝም መርህ የፖለቲካ አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን እውን ለማድረግ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ወጣት መሪዎችን ማፍራት ተገቢ ነው።