ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ይሰራሉ-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችላቸውን የዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተሰናባቿ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደሯ በቆይታቸው የኢትዮጵያ እና አውስትራሊያን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሁለትዮሽ ትብብሩን መደበኛ የፖለቲካ ምክክሮች እና የከፍተኛ ባለስልጣናት የጉብኝት ልውውጦች በማድረግ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ አመልክተዋል።

አምባሳደር ጁሊያ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቆይታቸው ወቅት ላደረገላቸው ድጋፍ እና ትብብር ምስጋና ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጁሊያ ኒብሌት ከእ.አ.አ 2021 አንስቶ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም