የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ሽብርተኝነት እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ሽብርተኝነት እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመከላከል ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ሽብርተኝነት፣ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ መረጃ በመለዋወጥ በጋራ ለመከላከል ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ የፖሊስ ለፖሊስ ግንኙነታችውን ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ዛሬ ተፈራርመዋል።
በፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ መስሪያ ቤት የተደረገውን ስምምነት የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ ናቸው።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ፥ በሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ያሉ የቴክኖሎጂ እና ሌሎች አቅሞችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ እና በሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ አካዳሚ ወጣት የፖሊስ ኦፊሰሮችን ለማሰልጠንና ልምድ ለመለዋወጥ መግባባታቸውን አመልክተዋል።
አያይዘውም፥ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ ትብብር መድረክን በጋራ ለማጠናከር እና ከምስራቅ አፍሪካም ባለፈ እንደ አፍሪፖል ያሉ ተቋማትን ለማጠናከር በጋራ ለመስራት መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በ2025 በሚካሄደው የኢንተርፖል ፕሬዝዳንት ምርጫ ላይ እንደ አፍሪካ እጩ ተወዳዳሪ በጋራ ለማዘጋጀት፤ የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እና ተቀናጅተው ለመሥራት መስማማታቸውንም እንዲሁ።
ስምምነቱ በቅርቡ ወደ ተግባር እንዲቀየር ከሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት የተቀናጀ ቴክኒካል ቲም መደራጀቱን ገልጸው ስምምነቱ በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባም አክለዋል።
የሩዋንዳ ብሔራዊ ፖሊስ ኢንስፔክተር ጀነራል ፌሊክስ ናሙሆራንዬ ተቋማቸው ለስምምነቱ ትግበራ እና ስኬታማነት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ማዕቀፉ የሁለቱ ሀገራት ደኅንነትን ለማረጋገጥ አስተዋፅኦ ከማድረጉም ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እና ለተቀረው ዓለም የድርሻውን እንደሚወጣ መናገራቸውን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።