የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቷል-የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ):-የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንዲሆን ትኩረት መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሐኪም ሙሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ያሉት ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በተፈራረመበትና የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ኤሌክትሮኒክ የተግባቦትና የመረጃ ልውውጥ ስርዓት (E-PPD) ይፋ በሆነበት መድረክ ላይ ነው።
አብዱልሐኪም ሙሉ (ዶ/ር)፤ የመግባቢያ ስምምነቱ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርቦ የመስራት ባህልን ለማዳበር የሚያስችል መሆኑን ገልፀው፥ጠንካራ የልማት አጋርነት እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በፖሊሲ፣ በሕግ አፈፃፀም እንዲሁም በአሠራር ስርዓት ምክንያት የሚከሠቱ ንግድ ነክ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሚረዳ በመጥቀስ ለአፈፃፀሙ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደጉን ገልጸው፥ በቀጣይም የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዋነኛ አንቀሳቃሽ እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።
ይፋ የሆነው ኤሌክትሮኒክ የተግባቦት ስርዓትም መንግስትና የግሉ ዘርፍ በቅርበት እየተገናኙ ምክክርና ውይይት በማድረግ ችግሮችን በጋራ የሚፈቱበትና መረጃ የሚለዋወጡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሰብስብ አባፊራ በበኩላቸው፤ምክር ቤቱ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል እንደ ድልድይ የሚያገለግል ነው ብለዋል፡፡
የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የኤሌክትሮኒክ የተግባቦትና የመረጃ ልውውጥ ስርዓትም የምክር ቤቱን ሚና የሚያጎለብት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡