ከተለምዷዊ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የተሻገረው የኢትዮ-አልጄሪያ ወዳጅነት - ኢዜአ አማርኛ
ከተለምዷዊ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የተሻገረው የኢትዮ-አልጄሪያ ወዳጅነት

የኢትዮ-አልጄሪያ ግንኙነት ታሪካዊ ነው፡፡ታሪካዊነቱ በዘመንም፣ በጸና ወዳጅነትም ይለካል።ትናንት ማምሻውን የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ የሀገሪቷን ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔን መልክዕት ይዘው አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
ዛሬ ማለዳ ደግሞ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የፀና ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናግረዋል። የፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔን መልዕክትም ተቀብለዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ የሰሜን አፍሪካዊቷ አልጄሪያ እና የኢትዮጵያን ወዳጅነት የትመጣ እና ሂደት በወፍ በረር እንቃኝ።
የኢትዮ-አልጀሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሰባት አስርት ዓመታትን ተሻግሯል። ሁለቱ ሀገራት ከመደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የተሻገረ ወንድማማችነትና ወዳጅነት መስርተዋል።
የፈረንሳይ ቅኝ ተገዥ የነበረችው አልጄሪያ በአውሮፓዊያኑ 1960ዎቹ መባቻ ነጻነቷን ለመቀዳጀት ትንቅንቅ ላይ በነበረችበት ዘመን ኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች። ይህን ደግሞ በኢትዮጵያ የአልጄሪያ አምባሳደር የነበሩት ኤልሃምዲ ሳላህ ‘አልጀሪያ የኢትዮጵያን ውለታ አትረሳውም’ ሲሉ በአውሮፓውያኑ 2022 ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀው ነበር።
አልጀሪያ በ1962(በአውሮፓዊያኑ) ነበር ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ያረጋገጠችው። ከዚህ ዘመን ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት ወዳጅነታቸውን መሰረቱ። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት እና የፓን አፍሪካኒዝም እንዲያብብ ንቅናቄ አድርገዋል። በ1960ዎቹ መጨረሻም ይፋዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን በይፋ ጀመሩ።
አልጄሪያ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት(የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በ1976(እ.ኤ.አ) ከፈተች። ኢትዮጵያም በ2016 ኤምባሲዋን በአልጀርስ ከፍታለች።
ሁለቱ ሀገራት በአውሮፓዊያኑ 2014 በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድ፣ ባህል እና በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችል የጋራ ኮሚቴ ፈጥረዋል። ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት ጥበቃ እና ማስተዋወቅ እንዲሁም ተደራራቢ ታክስ ማስቀረትን ጨምሮ ከ20 በላይ የትብብር መስኮች በጋራ መስራት ስምምነት ተፈራርመዋል። ከሁለትዮሽ ባሻገርም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የትብበር መስኮች ያላቸውን ትብብር የማጠናከር ፍላጎት አላቸው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም በኒውዮርክ በተካሄደው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸው ይታወቃል። በዚሁ ውይይት ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን አልፎም በዓለም የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
አምስተኛውን የኢትዮ-አልጄሪያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በቅርብ ጊዜ ለማከናወን የተጀመረውን ዝግጅት ለማፋጠን ተስማማተዋል።
አልጄሪያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ከአውሮፓዊያኑ ጃንዋሪ 2024 አንስቶ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በመስራት ላይ ትገኛለች። ይህም ሁለቱ ሀገራት በባለብዝሃ ወገን የዲፕሎማሲ መድረክ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ የሚያጎለብት ነው።
አልጄሪያ በአውሮፓዊያኑ በ2021 የአረብ ሊግ ሊቀመንበር በነበረችበት ወቅት ተቋሙ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተዛባ አረዳድ ለማስተካከል እና ሚዛናዊ እይታ እንዲኖረው ጥረት አድርጋለች።
የኢትዮ-አልጄሪያ የሁለትዮሽ ትብብር የሚያጠናክሩ የጉብኝት ልውውጦች እና ውይይቶች እያደጉ መጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም በአልጄሪያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወቃል። በወቅቱም ከአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ጋር ተወያይተው ነበር።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የኢትዮ-አልጄሪያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ በሁለትዮሽ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚቻለባቸው ዘርፎች እንዳሉ ገልጸው ነበር።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በሀገራቱ መካከል የጉብኝት ልውውጦች እና ውይይቶች እየጨመሩ መጥተዋል።
ለአብነትም በአውሮፓዊያኑ በ2021 የያኔው የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራምታኔ ላማምራ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ነበር፤ የሁለትዮሽ ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም አይዘነጋም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ደግሞ በሩሲያ ሶቺ በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ከተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ-ሩሲያ የትብብር ፎረም የሚኒስትሮች ስብስባ ጎን ለጎን ከአልጄሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ጋር መክረዋል። በውይይታቸውም የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያስጠብቁ ቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። እናም ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ የትብብር መስኮች ግንኙነታቸውን ማጎልበት ቀጥለዋል።
በአልጄሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሀመድ ዋሬ በቅርቡ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለአልጄሪያው ፕሬዝዳንት አብዱልመጂድ ቴቡኔ ሲያቀርቡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ልባዊ ሰላምታ እና የወዳጅነት መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።
ዛሬ ደግሞ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የአልጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ የፕሬዝዳንት አብደልመጂድ ቴቡኔን መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አድርሰዋል።
የሚኒስትር አሕመድ አታፍ ጉብኝት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው እና የኢትዮ-አልጀሪያ ሁለትዮሽ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት አካል ስለመሆኑ የአልጄሪያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ አታፍ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጋርም ተወያይተዋል። በውይይቱ በሁለትዮሽ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው አገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ትስስር በማጠናከር እና አዳዲስ የትብብር አድማሶችን በመፈለግ አጋነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እና አልጄሪያ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብስባን በቅርቡ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
እናም ኢትዮጵያና አልጄሪያ ከተለምዷዊ ዲፕሎማሲያዊ ትብብር የተሻገረ ነው። ሁሉን አቀፍ በሆኑ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ ትብብር መስኮች እየተወዳጁ ነው። የስትራቴጂካዊ አጋርነት ደረጃ እየጎለበተ ይመስላል። የአገራቱ መጻዒ የትብብር ጊዜ ብሩህ እና ፍሬያማ እንደሚሆን አያጠራጥርም።