በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንጽሕና አጠባበቅ ባህልን በማጎልበት ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የንጽሕና አጠባበቅ ባህልን በማጎልበት ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው

ዲላ፤ ታህሳስ 7 /2017 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግልና የአካባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ባህልን በማጎልበት ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
"ንጹህ እጆች ለጤናችን ዋስትና ናቸው" በሚል መሪ ሀሳብ የዓለም የእጅ መታጠብ ቀን በክልል ደረጃ ጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ወረዳ ሀሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ተከብሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ በወቅቱ እንዳሉት፤ በተለይ ምግብ ከማዘጋጀት፣ ከመመገብ በፊት እና ከመጸዳጃ ቤት መልስ እጅን መታጠብ ለጤነኛ ኑሮ መሠረታዊ ነው።
በዚህ ረገድ በክልሉ የግልና የአከባቢ ንጽሕና አጠባበቅ ባህልን በማጎልበት ተላላፊ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል አቅጣጫ ተይዞ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በጤናና በትምህርት ተቋማት እንዲሁም ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች የመጸዳጃ ቤቶችና የማመቻቸትና ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዓለም የእጅ መታጠብ ቀንም የዚሁ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በተለይ የመጸዳጃ ቤት ደረጃና ሽፋን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል ።
ሆኖም እጅ የመታጠብ ባህል ዝቅተኛ መሆን በክልሉ ለተላላፊ በሽታዎች በተለይ ለ" ታይፎድ" ለአንጀት ጥገኛ ትላትልና የተቅማጥ ተጋላጭነት ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ የባህሪ ለውጥ በማምጣት እጁን ሁል ጊዜ በአግባቡ በመታጠብ ተላላፊ በሽታዎችን ለመግታት የሚደረገው ጥረት እንዲያግዝ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በተሻሻለና ደህንነቱ በተጠበቀ መጸዳጃ ቤት መጠቀም ክብርም ዘመናዊነትም ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ አንዱአለም ማሞ ናቸው።
በዞኑ በቤተሰብ ደረጃ የመጸዳጃ ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፊ ውሃ እንዲኖራቸው በማድረግ የአካባቢና የግል ንጽህናን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር ተወካይ አቶ ተካልኝ በቀለ በበኩላቸው፤ በወረዳው ባለው የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት የግል ንጽሕና አጠቃቀም ላይ ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል።
ምንጭ ማጎልበትን ጨምሮ በሌሎችም አማራጮች የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረቱን በማቃለል የግል ንጽሕና አጠቃቀምን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም የእጅ መታጠብ ቀን በተለያዩ የግንዛቤና የእጅ መታጠብ መርሃ ግብሮች የተከበረ ሲሆን፤ በየደረጃው የሚገኙ የጤናው ዘርፍ አመራር አባላት፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች ተሳትፈዋል።