ቀጥታ፡

መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየወሰደ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያ ለውጥ እያመጣ ነው - የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አሶሳ፤ ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ)፦ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየወሰደ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያ ለውጥ እያመጣ መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ የትውውቅ መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፤ በዚሁ ወቅት የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ የግብርናውን ዘርፍ በሁሉም መስክ ለማሻሻል የሚያግዝ ነው ብለዋል።


 

ፍኖተ ካርታው የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ፣ ሰፋፊ የግብርና ስራዎች እንዲከናወኑ እና አርሶ አደሩ ከምግብ ዋስትና በተጨማሪ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው ድርሻ ከፍ እንዲል ያደርጋል ነው ያሉት።

መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እየወሰደ ያለው የፖሊሲ ማሻሻያ ለውጥ እያመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ፍኖተ ካርታው በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በተጠና መልኩ የግብርና ውጤቶችን ለማምረት የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ፍኖተ ካርታው የግብርና ስራን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።


 

አርሶ አደሮች አዋጭ እና ተስማሚ የሆኑ የግብርና ምርቶች ላይ በስፋት አንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።

ክልሉ ሰፊ የእርሻ መሬት ባለቤት መሆኑን ጠቁመው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማልማት የተያዘውን ጅምር ስራ የበለጠ ለማሳደግ ፍኖተ ካርታው ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።

ፍኖተ ካርታው ወደ ስራ እንዲገባ አመራሩ በቅንጅት መስራት እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ለ10 ዓመታት ተግባራዊ ለሚደረገው የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተስማሚ ይሆናሉ የተባሉ 14 የሰብል ዓይነቶች መለየታቸው በመድረኩ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የፌዴራል የዘርፉ አመራሮች እና ባለሙያዎች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም