የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫ ፕሮጀክት ነው - አቶ ገብረመስቀል ጫላ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫ ፕሮጀክት ነው - አቶ ገብረመስቀል ጫላ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫ ፕሮጀክት ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራ ዕድል ፈጠራ እና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት በአርባምንጭ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
አቶ ገብረመስቀል ጫላ ክልሉ 19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ዋንጫ መረከቡን አስታውሰው ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ሀብት የማሰባሰቡን ተግባር በመደገፍ አሻራውን ሊያሳርፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ግድቡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የይቻላል መንፈስ እንዲጎለብት ያደረገ ከመሆኑ ባሻገር ህዝቦች በመተባበር ከድህነት መውጣት እንደሚችሉ ያመላከተ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የትብብርና የአንድነት መገለጫ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ዘርፉ አጥናፉ ኢትዮጵያውን በራሳቸው አቅም እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግድብ ወደ መጠናቀቁ መድረሱን አመልክተዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በህዳሴ ግድብ ዋንጫ አማካኝነት እስከ አሁን ከ672 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት ማሰባሰቡን መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።