የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በጃፖን ካሳማ ከተማ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በጃፖን ካሳማ ከተማ ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 7/2017(ኢዜአ)፦ በጃፓን ኢባራኪ ግዛት ካሳማ ከተማ የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ እና 19ኛው የካሳማ ከተማ የግማሽ ማራቶን ውድድር ተካሂዷል።
ውድድሩ ትላንት መካሄዱን በቶኪዮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
ውድድሩን በአንደኝነት ላጠናቀቀው ተወዳዳሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ቶኪዮ ናሪታ የደርሶ መልስ የአየር ቲኬት እንዲሁም ሁለተኛ እና ሶስተኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎችም የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቷል።
በጃፓን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዳባ ደበሌ የግማሽ ማራቶን ውድድሩን ማስጀመራቸውም ተጠቁሟል።
የጃፖን መንግስት ይህን ውድድር በማዘጋጀቱና የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ መታሰቢያ በማድረጉ ምስጋና በማቅረብ መሰል ውድድሮች ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት መልካም ግንኙነት እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በስፖርቱ ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀው በከተማው የሚገኝ የስፖርት ቁሳቁሶችን የሚያመርት ኩባንያ ላደረገው የቅርጫት ኳስ ድጋፍም አመስግነዋል።
የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ በበኩላቸው ከተማው ከኤምባሲው ጋር እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና በቀጣይ አመት የሚደረገው የ20ኛ አመት መታሰቢያ ውድድር በከፍተኛ ደረጃ ለማዘጋጀት እንደሚሰሩ መናገራቸውም ተገልጿል።
እንዲሁም ከኢትዮጵያ ከተማ ጋር ጉድኝት በመመስረት በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ መግለጻቸውም ተመላክቷል።
በከተማዋ ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በቋሚነት እንዲታወስ በስሙ ጎዳና ወይም ፓርክ እንዲሰየምለት በአምባሳደር ዳባ ደበሌ የቀረበውን ጥያቄ እንደተቀበሉትና ከኤምባሲው ጋር ተባብሮ ቋሚ ማስታወሻ ለማኖር ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።