ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር በሀዋሳ ተጀመረ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 6/2017 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ  9ኛው ዙር ውድድር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀመረ ። 

በአስር ክለቦች መካከል የሚደረገው ውድድሩ የመጀመሪያውን ዙር ጨዋታዎች ለማስተናገድ በተመረጠችው በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የስፖርት ቤተሰቦች በተገኙበት ተጀምሯል።


 

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽንና የምስራቅ አፍሪካ ዞን አምስት ፕሬዚዳንት ፍትህ ወልደሰንበት (ዶ/ር) በመክፈቻ ስነ ስርአት ላይ እንደገለጹት አሁን ላይ ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤቶች  እየተመዘገቡ ነው።

በአፍሪካ መድረክም ሀገርን የሚወክሉ ክለቦች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አመልክተዋል።

ውድድሩ ሀገርን የሚወክሉ አቅም ያላቸውን ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ረገድ ከፍተኛ እገዛ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ  “ሴቶችን ወደ ስፖርት  መድረክ አለማምጣት፣ አዳዲስ ክለቦችን በውድድር አለማሳተፍና ሌሎች ተግዳሮቶች እንደሀገር ያልተሻገርናቸው ችግሮች ናቸው” ብለዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊና የሚኒስትሯ ተወካይ አቶ ሰለሞን አሊዩ በበኩላቸው "ስፖርት ጤናማ ዜጎችን ለመፍጠርና ለሰላምና አብሮነት ግንባታ ያለውን ሚና ለመጠቀም እየተሰራ ነው" ብለዋል።

ለዚህም የውድድር ስነስርዓት ተሳትፎና መሰረተ ልማትን ማጠናከርን ጨምሮ በሁሉም ዘርፍ ወጣቱ አቅሙን አውጥቶ ሀገርን ወካይ እንዲሆን ለማስቻል ሚኒስቴሩ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል ።

ተሳታፊዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ውድድራቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጀጎ አገኘሁ እንዳሉት በክልሉ ያለውን የስፖርት አቅም ለማጠናከርና ውድድሩ ያለውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል ።

ውድድሩ የስፖርት ቱሪዝምና የህዝቦች ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ጠቁመው ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል። 

ውድድሩ በሀዋሳ መካሄዱ ዘርፉንም ሆነ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እንዲሁም የህዝቦችን አብሮነትና ትስስር ለማጠናከር  ጉልህ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አገና ናቶ ናቸው።

አስተዳደሩ ለውድድሩ ስኬት የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አስታውቀዋል ።

በውድድሩ ሻምፒዮን ለመሆን በቂ ዝግጅት አድርገው መምጣታቸውን የገለጹት የመቀሌ 70 አንደርታ የእጅ ኳስ ቡድን አሰልጣኝ አማኑኤል ስዩም፤ ውድድሩን  በጥሩ ሁኔታ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ ለውድድሩ ፌዴሬሽኑም ሆነ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባደረጉት ዝግጅት ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኦሜድላ እጅ ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ  ተስፋዬ ሙለታ ናቸው።

በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም