ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የሚከናወኑ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2017(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በከተማችን ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነት ከምናካሂዳቸው የቤት ግንባታ መርሃ ግብር ትልቁ የሆነው የኦቪድ ገላን ጉራ ሳይት 60 ሺሕ ቤቶች ግንባታ፣ በለገሀር ጊፍት ሪልስቴት የሚገነባቸው 4 ሺህ 370 ቤቶች የግንባታ ሂደትን እንዲሁም በቦሌ ሩዋንዳ በግሉ ዘርፍ እየለሙ የሚገኙ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ጎብኝተናል ሲሉ አስፍረዋል።
በምናካሂዳቸው የልማት ስራዎች ቅድሚያ ለልማት ተነሺዎች በማለት በጀመርነው አሰራር መሰረት የኦቪድ ገላን ጉራ ሳይት ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች የሚሆኑ 770 ደረጃቸውን የጠበቁ ምትክ ቤቶችን ቅድሚያ ሰጥተን ግንባታቸውን በማፋጠን ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዚህ የገላን ጉራ ፕሮጀክት ከሚገነቡ ቤቶች ውስጥ ኮንዶሚኒየም በመቆጠብ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ የምንገኝ ሲሆን በከተማችን ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ከግሉ ዘርፍ ጋር በመተባበር የጀመርናቸውን ስራዎች ከመሰረተ-ልማትና ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቅረፍ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።