ኢትዮጵያ ለስኬታማ ድል የበቃችው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት በመተግበሯ ነው- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለስኬታማ ድል የበቃችው ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት በመተግበሯ ነው- ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)
የመንግስት ኮሙኒኬሸን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ ኢትዮጵያ በ2024 በጠቅላላ ሃገር ውስጥ ምርት ኢትዮጵያ ከአምስቱ የአፍሪካ ምርጦች ውስጥ አንዷ ሆና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መመረጧን አስታውሰዋል።
"ለዚህ ስኬታማ ድል የበቃችውም ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ አቅጣጫ በመከተል፣ ለየኢኮኖሚ ዘርፎቹ የተስተካከለ አቅጣጫና ስትራቴጂ በማስቀመጥ እና በብቃት መተግበር በመቻሏ ነው" ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ በመኸር አዝመራ፣ በበጋ መስኖ እና በበልግ አዝመራ ስንዴን ጨምሮ ለአምስት ዋና ዋና ሰብሎች የተለየ ትኩረት በመስጠት ምርታማነትን በጥራትና በመጠን መጨመሯን ጠቅሰዋል።
"ከሀገራችን እና ከዘርፎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ ፕሮግራሞች በመንደፍ በተገቢው መንገድ በመተግበር ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል" ብለዋል።
ከሰሞኑ በተለያዩ ክልሎች ባደረጓቸው ጉብኝቶችም በየአካባቢው ያሉ ጸጋዎችን ለመግለጥና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ እንዲሁም ለሌሎች አካባቢዎችም ትምህርት የሚሰጡ ስራዎች እንደተከናወኑ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም በአርባ ምንጭ እና አካባቢው በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በምስራቅ ጉጅ በወርቅ ልማት፣ በምዕራብ ጉጅ በዘመናዊ የቡና ልማት፣ በሀዋሳ የኮሪደር ልማት እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ከፍ ያለ የልዕልና መንገድ መጀመሩን የሚያሳዩ እና የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ትክክለኛነት የሚያንፀባርቁ ናቸው ብለዋል።
ከትናንት ጀምሮ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ባደረጉት ጉብኝትም በሚዛን አማንና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች እጅግ አመርቂ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ በክላስተር የለማ የበቆሎ ሰብል፣ የንብ ማነብ ስራ፣ በክላስተር የለማ የቡና ማሳ፣ የሙዝ እርሻ እና የቡና መፈልፈያ ስራዎችን መመልከታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት በክልል ከተሞች መቀጠሉን በመጥቀስ፤ የኮሪደር ልማት ጠንካራ የማህበረሰብ ፍቃደኝነት፣ ተሳትፎና የባለሃብቶች ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ የአመራሩ እረፍት አልባ እና እንቅልፍ የለሽ ትጋትና የቅርብ አመራር ይጠይቃል ነው ያሉት።
'የዘመነ ከተማ የስልጡን ማህበረሰብ መገለጫ ነው' ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ ሚዛን አማን የገዘፈ የኮሪደር ስራ መጀመሯን በእጅጉ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
ሚዛን አማን በሌማት ቱሩፋት በተለይ በወተት ምርት፣ የማር ልማት፣ በዶሮ ልማት በቤተሰብ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ ያለበት ገበታዋን እየሞላች መሆኑንም እንዲሁ።
"ከሰሞኑ የተግባር ውጤትን የሚገልጡ፣ የኢትዮጵያን ልዕልና የሚያረጋግጡ፣ ብልጽግናችንን ከሚጨበጥ ተስፋ ወደ አፍሪካ ተምሳሌት የሚያሳድጉ የልማት ሥራዎችን መሬት ላይ አይቻለሁ" ብለዋል።