በክልሉ በሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሂደት የተሳሳተ መረጃ የሰጡ አካላት በሕግ ተጠያቂ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሂደት የተሳሳተ መረጃ የሰጡ አካላት በሕግ ተጠያቂ ይደረጋሉ
ሚዛን አማን፤ ታኅሣሥ 6/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሂደት የተሳሳተ መረጃ የሰጡ አካላት በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ተግባር ከሙስና መከላከል ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ ነው።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የአራት ሺህ አመራሮችና ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ተቋማት ሠራተኞችን ሀብት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ምዝገባውን ተከትሎ ከሕዝብ የመጡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በተደረገው የማጣራት ሂደት ምንጩ ያልታወቀ ሀብት መሸሸግ ወይም ያለማስመዝገብ እንዲሁም የሌለን ሀብት የማስመዝገብ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ማረጋገጡን ተናግረዋል።
በዚህም የተሳሳቱ መረጃዎችን አደራጅቶና ተንትኖ ለሚመለከተው የፍትሕ ተቋም ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል።
መረጃን ትክክለኛነት የማጣራት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው፤ ህብረተሰቡም መሰል መረጃዎችን ለኮሚሽኑ በመጠቆም የነበረውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ጎዴቶ በበኩላቸው እንደ ክልል ለሙስና ወንጀሎች መከላከል የሚደረጉ ጥረቶች ከግብ እንዲደርሱ ቢሮው የራሱ አቃቤ ሕግ በመመደብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ የተገኘ የመንግስት አመራር ሆነ ባለሙያ ሀብቱ እስከ መወረስ የሚያደርስ አዋጅ እንዳለ ቢሮ ሀላፊው አስታውሰዋል።
ማንኛውም አካል የወንጀል ጉዳዩ ተጣርቶ ጥፋተኛ ከሆነ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በሕግ ፊት ቆሞ እንዲዳኝ ከማድረግ አኳያ ቢሮው ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።