ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን ከ290 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማ ሰብል ተሰበሰበ

ደሴ፤ ታህሳስ 6/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ወሎ ዞን በመኸር እርሻ ከለማው ሰብል እስከ አሁን ድረስ ከ290 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ ባለፈው የመኸር ወቅት 432 ሺህ ሄክታር መሬት ለምቷል።

ከዚህም 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፣ እስከ አሁን በዘመቻ በተደረገ እንቅስቃሴ ከ290 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።


 

በዚህም በቆሎ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ማሾ፣ ቦለቄ፣ ምስር፣ አተር፣ ገብስና ሌሎች ሰብሎችን ለመሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጹት።

የሰብል አሰባሰብ ሥራውን ከብክነት የጸዳ ለማድረግም በአጨዳ፣ በአከማመር፣ በመውቃትና ወደ ጎተራ በማስገባት ሂደት ተገቢ ጥንቃቄ መደረጉን አስረድተዋል።

በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎችም የሰብል አሰባሰቡን ተግባር ለማፋጠንና የምርት ብክነትን ለመቀነስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መሰራቱንም አቶ ይመር ገልጸዋል።

በዞኑ የተሁለደሬ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጀማል አህመድ በበኩላቸው፣ በሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ያለሙት ጤፍ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ማሾ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳይበላሽ ቀድመው መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።

በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን በቆሎ፣ ጤፍና ማሽላ በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ፈጥነው መሰብሰባቸውን የገለጹት ደግሞ በአርጎባ ወረዳ የቀበሌ 7 ነዋሪ አርሶ አደር ሰይድ አሊ ናቸው።

በቀጣይ ከአውድማ ዝግጅት ጀምሮ በመውቃትና ምርቱን በማጓጓዝ ሂደት የምርት ብክነት እንዳይከሰት በጥንቃቄ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በመኽር እርሻ ከለማው መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም