370 ኪሎ ዋት ማመንጨት የሚችል የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
370 ኪሎ ዋት ማመንጨት የሚችል የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመረቀ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 6/2017 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን መደወላቡ ወረዳ በ195 ሚ ብር ወጪ የተገነባውና 370 ኪሎ ዋት ማመንጨት የሚችለው የኦዳ ሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመረቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢ/ር ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር) በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ኦዳ ሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 15 ሺ የገጠር ነዋሪዎችን የኃይል ተጠቃሚ ያደርጋል።
ፕሮጀክቱ በገጠርና በከተማ የሚከናወኑ የልማት እንቅስቃሴዎችን የሚደግፍና ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአካባቢው ህብረተሰብ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት መንፈስ መጠበቅና የጋራ ሀብት አጠቃቀም ልምድ ማዳበር እንደሚገባው ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ በበኩላቸው የመብራት አገልግሎት በዘላቂነት ለመጠቀም መሰረተ ልማቱን በአግባቡ መጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ፕሮጀክቱ የተገነባው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ በጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር፣ በአውሮፓ ሕብረት እና በኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ትብብር ነው።