ቀጥታ፡

በቤንች ሸኮ ዞን በክላስተር እየተከናወነ ያለው የግብርና ልማት ስራ ውጤታማ ነው

ሚዛን አማን፤ታኅሣሥ 5/2017 (ኢዜአ):-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን በክላስተር እየተከናወነ ያለው የተለያየ የግብርና ልማት ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራ እንቅስቃሴዎችን ተመልክተዋል።

ከተመለከቷቸውም መካከል በደቡብ ቤንች ወረዳ 13 ቀበሌዎች በክላስተር የሚያመርቱት የሙዝ ልማት ይገኝበታል።

በወረዳው የመኸር እርሻ የለማው የካሹ በቆሎ ክላስተር ሌላው የተመለከቱት የልማት ስራ ነው።

የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በወቅቱ እንዳሉት፤ የጃንቹ ሙዝ ክላስተር ከ500 በላይ አርሶ አደሮችን አቅፏል።

453 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የሙዝ ልማት ሥራ ከ2012 ጀምሮ ቀጥሉ እንደለ አመልክተው፤ ከዚህም ከፍተኛ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ በየቀኑ እየተላከ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ በክላስተር እየተከናወነ ያለው የተለያየ የግብርና ልማት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የደቡብ ቤንች ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኪዳኔ ሺቅ፤ ባለፈው የመኸር ወቅት በወረዳው ከለማው 12 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ አራት ሺህ ሄክታሩ በክላስተር የለማ ነው ብለዋል።

በወረዳው በቆሎ ፣ቡና፣ የንብ ማነብ፣ የሽንኩርትና ሌላም የግብርና ልማት በክላስተር የማከናወን ልምድ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ከክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራር አባላት ጋር በመሆን የሌማት ትሩፋት፣ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የሆነው የደንቢ ሎጅ የሥራ አፈጻጸምንም ተመልክተዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም