የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ድጋፍ ይደረጋል- ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ድጋፍ ይደረጋል- ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ
ባህርዳር፤ ታኅሳስ 5/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የልማት ድርጅቶች ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ ድጋፍና ክትትል እንደሚደርግ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አስታወቁ።
የክልሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሥራ አስፈፃሚዎች በቢዝነስና አመራር ጥበብ ስልጠናና የልምድ ልውውጥ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።
የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ የልማት ድርጅቶቹ የመንግሥትን የልማት ክፍተት በመሙላት አስተዋጾ ሲያበረክቱ ቆይተዋል።
በተለይም የክልሉን ገቢ በማሻሻል፣ የሥራ እድል በመፍጠር፣ መስረት ልማትን በማስፋፋትና መስል የልማት ተግባራትን በማከናወን የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ማገዛቸውን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ድርጅቶቹ ከመንግስትና ህዝብ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ ከማሳካት አንፃር ክፍተቶች እንዳሉባቸው ተናግረዋል።
በዚህም አብዛኞቹ ትርፋማ ከመሆን ይልቅ ለኪሳራ ሲዳረጉና ከመንግሥት ድጎማ ሲጠይቁ ይስተዋላል ብለዋል።
የድርጅቶችን አመራርና አስራር በንግድ ሥራ ህጎች ላይ መሰረት በማድረግ ወደ ተሻለ ትርፋማነት እንዲመጡና የሚጠብቅባቸውን የልማት ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለዚህም ውጤታማነት የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ድጋፋና ክትትል እንደሚያደርግ ርዕስ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው ጌቴ በበኩላቸው፤ በክልሉ የህዝብን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 46 ድርጅቶች በተለያዩ የልማት ዘርፎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።
የልማት ድርጅቶችን የሥራ እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግም በተማከለ አስተዳደር ወደ አንድ እንዲመጡ የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።
በአማራ ክልል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የመንግሥት ድርጅቶች አስራራቸውን በማዘመን የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደሚደርጉ የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶከተር ብሩክ ታየ ናቸው።
በመድረኩ የአስራር ጥንካሬዎችን የበለጠ ማጎልበትና ክፍተቶችን ማስተካከል የሚያስችል የልምድ ልውውጥና ሥልጠና ተሰጥቷል።
በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎችም አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።