ቀጥታ፡

11ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ 11ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት በታላቁ ቤተ-መንግስት በመካሄድ ላይ ነው።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ብቁ የሆኑ የምርትና አገልገሎት ሰጪ ድርጅቶችም የጥራት ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ይጠበቃል።

በ11ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር በተለያዩ መንገዶች ጥሪ ከተደረገላቸው ድርጅቶች እና ተቋማት ውስጥ 50 ድርጅቶች ተመዝግበው እስከ ውድድሩ መጨረሻ ዘልቀዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የተቋቋመው በ2000 ዓ.ም ነው።

ዓላማውም ለጥራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የሽልማት ስርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን አለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ብቃት ማሳደግ እና የጥራት ጽንሰ ሐሳብን በማስረጽ ጥራት የሀገሪቱ ባህል እንዲሆን ማገዝ ነው።

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴን ጨምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር)፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም