የኦሮሚያ አብዲ ቦሩ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል አገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ አብዲ ቦሩ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል አገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፤ታኀሳስ 5/2017(ኢዜአ)፥ የኦሮሚያ አብዲ ቦሩ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል አገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዚዳንት ሸኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ድጋፍ በሸገር ከተማ መልካ ኖኖ ክፍለ ከተማ የተገነባው የኦሮሚያ አብዲ ቦሩ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከል ተመርቆ ተከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ማዕከሉ ወላጅ የሌላቸውንና በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን ከማሳደግ ባሻገር የሁለቱን ወዳጅ አገሮች ትብብር ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
በምረቃው ወቅት ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት፥ ለምረቃ የበቃው ማዕከል የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል።
''ፕሬዝዳንት ሸኽ መሀመድ ቢን ዛይድ አልናህያን ትልቅ ስጦታ ነው የሰጡት፤ ግንባታውም ጥራቱን ጠብቆ የተከናወነ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።
ማዕከሉ በውስጡ ለሚያድጉ ህጻናት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ጠቅሰው ''ለዚህም በራሴና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቀርባለሁ'' ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አቅጣጫ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች 15 ሺህ 332 ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን በተገነቡ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችም ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ህጻናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ይህም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥና ትውልድን በመገንባት ረገድ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ በተጨባጭ እያየን ነው'' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በዚህ ዓመትም አምስት ሺህ ተጨማሪ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ ገልጸዋል።
ክልሉ ከዚህ በጎ ስራ ትምህርት በመውሰድ ሌሎች መሰል ማዕከላትን በማስፋፋት በትምህርት ዘርፍ ያለውን ችግር በማቃለል ቀጣይ ትውልድን ለማዘጋጀት ርብርብ ማደረግ ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምረቃው ወቅት ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጓዳኝ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ወገኖችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ለአብነትም ማዕድ ማጋራት፤ የአቅመ ደካማና አረጋዊያን ዜጎችን ቤት ማደስ፤ ለአይነ ስውራን የሚውል ትምህርት ቤት ግንባታና ሌሎች መሰል የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ነው ያብራሩት፡፡
በዛሬው እለት ለምረቃ የበቃው የህጻናት ማሳደጊያ ማዕከልም በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን የመደገፍ ስራ አካል መሆኑን ነው ያነሱት፡፡