ቀጥታ፡

የአንካራ ስምምነት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሠላም አምባሳደርነቷን ያሳየችበት ነው- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017 (ኢዜአ)፦ በአንካራ የተደረገው ስምምነት ችግሮችን በድርድር በመፍታት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የሠላም አምባሳደርነቷን ያሳየችበት መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰውን የአንካራ ስምምነት አስመልክቶ ከክልሉ አመራሮች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

አቶ አሻድሊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በምክክር የመፍታት ባህሏን ለዓለም ያሳየችበት ነው።

የአንካራው ስምምነት እንደ አገር የተጀመረውን ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የቀጣናውን ሠላምና ደህንነት ለማስከበር ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወኗን አውስተዋል።


 

የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄን ለመመለስ ረጅም ርቀት መኬዱንም ለማሳያነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰከነ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እያደረገች ያለው ጥረት በአፍሪካ ቀንድ የሠላም አምባሳደርነቷን ከፍ አድርጎ ያሳየ ነው ብለዋል።

የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ለዘመናት የዘለቀ ወንድማማችነትን እንደሚያጠናክር አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

ስምምነቱም የዘመናት የባህር በር ጥያቄ እውቅና የሰጠ መሆኑም ገልጸዋል።

የዛሬው ትውልድ ስምምነቱ ታሪካዊ እና ህጋዊ መሆኑን በመረዳት ሀገራዊ መተሳሰብና መግባባት ላይ የተመሰረተ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም