ማህበሩ ለሱዳን ስደተኞች እያደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ አለም አቀፋዊነቱን ያስመሰከረ ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለሱዳን ስደተኞች እያደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ አለም አቀፋዊነቱን ያስመሰከረ ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፥የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለሱዳን ስደተኞች እያደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ አለም አቀፋዊነቱን ያስመሰከረና የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦችን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ይህን ያሉት ዛሬ በማህበሩ 20ኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ነው።
ማህበሩ በኢትዮጵያ የፈተና ጊዜ የተወለደና የሰብዓዊነት ፋይዳን በመኖር ያወቀ መሆኑንም ነው በዚሁ ጊዜ ያነሱት።
ባለፉት 90 ዓመታት በኢትዮጵያ ለተከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች አፋጣኝ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ትልቅ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።
ማህበሩ በሱዳን የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመጡ የአገሪቱ ስደተኞች እያደረገ ያለው ሰብዓዊ ድጋፍ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የበለጠ በማጠናከር በኩል ጉልህ ሚና እንዳለውም ነው ፕሬዝዳንት ታዬ ያነሱት።
ማህበሩ በቀጣይም በመላ ሀገሪቱ ተዳራሽነቱን በማስፋት ከሰብዓዊ ድጋፎች ባለፈ ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ለዚህ ደግሞ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ነው ያረጋገጡት።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ፤ በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ዓመታትን የተሻገረ መሆኑን ገልጸው ይሕንንም አጠናክሮ ለመቀጠል ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ንቅናቄ መሰረታዊ መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ ለሚሆኑ ሰዎች የህይወት አድን ስራ ከማከናወን በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
የማህበሩ ያለፉት ሦስት ዓመታት ዓመታዊ ገቢ 3ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ለ16 ሚሊዮን ዜጎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ፣ በአደጋ ሥጋት ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ማህበሩ በነፃነትና በገለልተኝነት ስራውን እንዲከውን መንግስት በየዓመቱ ሲያደርግ የነበረውን የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ማሳደጉንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ እየታዩ ያሉ ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ ድርጊቶች ለመቅረፍና ቀጣዩ ትውልድም በስነ-ምግባር እና በሰብዓዊነት መርሆዎች የታነፀ እንዲሆን ''የሰብዓዊነት ትምህርት ቤት''ማቋቋሙንም ጠቅሰዋል።
ሰብዓዊ አገልግሎቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ሁሉም አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሚገኙት ከ80 በላይ የመድኃኒት መደብሮቹ አማካኝነት በዓመት 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እያቀረበ ይገኛልም ነው ያሉት።