እየተቀዛቀዘ ለመጣው ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ማተኮር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
እየተቀዛቀዘ ለመጣው ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ማተኮር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ እየተቀዛቀዘ ለመጣው ሰብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ አማራጮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተገለጸ።
በአለም አቀፍ ደረጃ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እየተበራከቱ ቢመጡም ለዚያ ምላሽ የሚሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች እየተቀዛቀዙ መጥተዋል።
ሰብዓዊ ድጋፎቹ ጎራ ለይተው እየተደረጉ ከመሆኑ ባለፈ የድጋፍ መሳሳትና ሽሚያ እንደሚታይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ያነሳሉ።
አለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ ከበጎነትና ከስብዕና ጋር ያለው የመርህ ትስስር እየላላ መሄዱንም ነው የሚናገሩት።
ይህ ክስተት ዝንባሌ ሳይሆን በተግባር እየታየ በመሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ተጎጂዎች ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝም አንስተዋል።
ኢትዮጵያም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያጋጠማትን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች በራሷ አቅም ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።
ይሁንና ከችግሩ ስፋት አኳያ የተራድኦ ድርጅቶች ድጋፍ ወሳኝ ቢሆንም ድጋፉ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ጸጋዎች በመጠቀም ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በራሷ አቅም ምላሽ ለመስጠት እየሰራች ያለውን ስራ በተመለከተ ኢዜአ ይጠይቃል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀ ማህበር የኦሮሚያ፣ የአማራና የትግራይ ክልሎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የስራ ሃላፊዎች ምላሽ አላቸው።
በዚህም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ መሀመድ ጀማል፣ በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ያሉ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም ከተረጂነት ለመውጣት እየሰራን ነው ይላሉ።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሻምበል ዋለ እንደሚሉት፣ ማህበሩ አብዛኛውን የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ያለው በተራድኦ ድርጅቶች እገዛ ነው።
ይህ ድጋፍ ቢቋረጥ የህብረተሰብ ልማት ስራዎች ሊቋረጥ የሚችል በመሆኑ የራስ አቅምን ማጠናከር ግድ ይላል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ማህበሩ ከአባላት ከሚሰበስበው ድጋፍ ባለፈ ህንጻዎችን በመገንባት እያከራየና ገቢ እያስገባ መሆኑን ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ብርሃን መኮንን በአለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ ድጋፎች እየተቀዛቀዙ መምጣታቸውን ይስማማሉ።
የሀገር ውስጥ አቅምን በማጠናከር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምላሽ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ ለማድረግ የራስ አቅምን ማጠናከር ላይ በትኩረት መስራት ለነገ የማይባል ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ስላሴ አለም አቀፍ ተራድኦ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ እንደ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ያሉ ተቋማትን ማጠናከር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።