ቀጥታ፡

በላሊበላ የገናን በዓልን ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦በየቅዱስ ላሊበላ ከተማ የገናን በዓል ለማክበር ለሚመጡ እንግዶች የተሟላ አገልግሎትና መስተንግዶ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የተለያዩ የሆቴሎች ስራ አስኪያጆች ገለጹ፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከ12ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ በንጉስ ላሊበላ አማካኝነት ከትልቅ ቋጥኝ ድንጋይ ከላይ ወደ ታች እና ከተራራ ጎን የተፈለፈሉት ድንቅ የኪነ ሕንጻ ውጤቶች ናቸው።

የኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጣኔና የላቀ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ማሳያ የዓለም የትኩረት ማዕከል በመሆን እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1970 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ባህልና ሳይንስ ተቋም /ዬኔስኮ/ የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የቅዱስ ላሊበላ 11ዱን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለመጎብኘት ከአራቱም የዓለም ማዕዘናት ወደ ኢትዮጵያ ይተማሉ፡፡

በተለይም በየዓመቱ ታህሳስ 29 ቀን የሚከበረው የገና በዓል እና "የቤዛ ኩሉ" መርሐ ግብር በቱሪዝም ልማት ለሚተዳደሩ የቅዱስ ላሊበላ ነዋሪዎች ታላቅ ገጸ በረከት ነው፡፡

የገናን በዓል ለሚታደሙ እንግዶች የተደረገውን ዘግጀት በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዘና ሪዞርትና ስፓ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብሩክ ሃይሉ፤ የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ቱሪዝም መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማዋ ቱሪዝም በተለይም በኮቪድ ወቅትና በሰሜኑ ጦርነት ጭምር ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ መነቃቃት እያሳየ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የገናን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ተቀብለን ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።

የላል ሆቴልና ስፓ ሥራ አስኪያጅ መብራቱ ሰማኝ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርሲቲያናት ከከተማዋ ህዝብ የገቢ ምንጭነት ባሻገር ሀገራዊ ትሩፋት ያላቸው የዓለም ቅርሶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች መቀዛቀዝ ገጥሞት የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ባለፉት ሁለት ወራት መነቃቃት አሳይቷል ብለዋል፡፡

ለዚህም ከተለያዩ የዓለም ሀገራትና ከሀገር ውስጥ የሚመጡ ጉብኝዎችን ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል፤አልጋዎቹም ቀድመው መያዝ ጀምረዋል ነውያሉት፡፡

የቤተ አብርሃም ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ዲያቆን አበበ ዓለሙ፤ የገናን በዓል ለማክበር በየዓመቱ የሚመጡ በርካታ ታዳሚዎች መኖራቸውን አስታውሰው ዘንድሮም ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

በመሆኑም ለክብረ በዓሉ ለሚመጡ እንግዶች ሁሉ ለአገልግሎትና መስተንግዶ የተሟላ ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም