ቀጥታ፡

የጀመርነው የግብርና ልማት ስራ ከተረጂነት እንድንወጣ እያገዘን ነው - የምስራቅ ባሌ ዞን አርሶ አደሮች

ጊኒር፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወኑት የግብርና ልማት ስራ ከተረጂነት እንዲወጡ እያገዛቸው መሆኑን የምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በባሌና ምስራቅ ባሌ ዞኖች የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

የስራ ሀላፊዎቹ ከጉብኝቱ በኋላ በሁለቱም የባሌ ዞኖች ያለውን እምቅ የልማት አቅም ለህዝብ ተጠቃሚነት ለማዋል በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ምስራቅ ባሌ ዞን በልማት ስራዎች ወደ ኋላ የቀረና ድርቅም በተደጋጋሚ የሚያጠቃው በመሆኑ ህዝቡም ለተረጂነት ተጋልጦ የቆየ እንደነበረ ተመልክቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች በተለይም በአካባቢያቸው ባለው የውኃ እጥረት እና ድርቅ ምክንያት ለተረጂነት ተዳርገው መቆየታቸውን ይናገራሉ።


 

በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ ከተቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲራጅ ሼህ ጣሂር፣ በውሃ እጥረት ምክንያት በግብርና ስራ ውጤታማ መሆን ሳይችሉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ግን መንግስት በአካባቢያቸው አነስተኛ ግድቦችን በመገንባቱ የግብርና ልማት ስራ በስፋት ማከናወን መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በግብርና ልማት ስራቸውም ከተረጂነት እየወጡ መሆናቸውን ጠቅሰው የበለጠ ለመለወጥ ትልቅ ተስፋ መሰነቃቸውን ነው የተናገሩት።


 

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሀመድ አህመደ ገዳ፣ ስምንት ሄክታር መሬት ቢኖራቸውም በውሃ እጥረት ምክንያት አልምተው ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአካባቢያቸው አነስተኛ ግድብ በመገንባቱ ያላቸውን መሬት በሙሉ በተለያዩ ሰብሎች ማልማት መጀመራቸውን ተናግረዋል።


 

በጊኒር ወረዳ የተሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጎሳ ጀማነህ በበኩላቸው ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ሙዝ፣ አቮካዶ እና በቆሎ በመስኖ እያለሙ፤ ህይወታቸው እየተሻሻለ መምጣቱን አስረድተዋል።

በመስኖ ልማት ስራው ኑሯቸውን በተሻለ መልኩ ከመደጎም አልፈው ለ18 ሰዎች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰው ለአካባቢው ገበያም አትክልትና ፍራፍሬ በብዛት እያቀረቡ እንደሆነ ገልጸዋል።


 

የምስራቅ ቦረና ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዘላለም አለማየሁ፤ ዞኑ ቆላማ እና የድርቅ ተጋላጭ በመሆኑ ህዝቡ ለተረጂነት ተጋልጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዞኑ የስንዴ ሰብል የማይታወቅበት እንደነበረ ያስታወሱት ኃላፊው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሰራው ስራ ስንዴ ለገበያ ጭምር ማቅረብ መጀመሩን እስረድተዋል።

ትናንት እርዳታ ሲጠበቅ የነበረው የአካባቢው ነዋሪ ዛሬ ከተረጂነት እየወጣ ሲሆን ዞኑም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሙሉ አቅም እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም