በውጭ ለሚገኙ ዜጎች እየተሰጠ ያለው የፓስፖርት አቅርቦት እየተሻሻለ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ ለሚገኙ ዜጎች እየተሰጠ ያለው የፓስፖርት አቅርቦት እየተሻሻለ መጥቷል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦በውጭ ለሚገኙ ዜጎች እየተሰጠ ያለው የፓስፖርት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮን መሪዎች እና አምባሳደሮች ገለጹ።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች ከመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙ የሚሲዮን መሪዎች፣ አምባሳደሮች እና የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ጋር በተቋሙ የሪፎርም ስራዎች ላይ የበይነ-መረብ ውይይት አድርገዋል።
የኢ-ፓስፖርት ያለበት ሂደት፣በተቀናጀ የድንበር አስተዳደር ስራ፣ በሰው ኃይል አደረጃጀት እና በተቋሙ በነበሩ ክፍተቶች ላይ የተደረጉ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች አስመለክቶ ውይይት ተደርጓል።
በአሰራሮች ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችም በውይይቱ ላይ ተነስተዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮን መሪዎች እና አምባሳደሮች ከዚህ ቀደም ከፓስፖርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የነበረ ከፍተኛ መዘግየት እንደነበረ አስታውሰዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ችግሩን ለመፍታት ያደረገው ሪፎርም ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
በመካከለኛ ምስራቅ አገራት የሚገኙ ዜጎች የፓስፖርታቸው የአገልግሎት ጊዜው ሲያበቃ ለከፍተኛ ችግር ተጋላጭ እንደነበሩ አውስተዋል።
አሰራሩ ዜጎች ውላቸውን አድሰው ያለ እንግልት ስራቸውን እንዲቀጥሉ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በተቋሙ የሪፎርም ስራ የመጡ ለውጦችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተቋሙ በቀጣይ ከሚሲዮን መሪዎች ጋር የሚያከናውናቸውን ስራዎች አስመልክቶ የስራ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።