ቀጥታ፡

እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያበስሩ ናቸው - ከንቲባ ከድር ጁሀር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያበስሩ ናቸው ሲሉ የድሬዳዋ ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ።

ከንቲባ ከድር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አመራር ሰጪነት የሚመራው የለውጥ ኃይል የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ያስቀመጣቸው ግቦች ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

የተገኙት ለውጦች እና የልማት ስኬቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያበስሩ ናቸውም ብለዋል።

በተርኪዬ ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር በስምምነት መጠናቀቁ ከሀገራቱ በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የሀገራቱ ህዝቦች በቋንቋ፣ በባህል እና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ስምምነቱ ለጋራ ብልጽግና በቁርጠኝነት አብሮ መስራት እንደሚያስችል ነው የተናገሩት።

የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው የአንካራው ስምምነት በዲፕሎማሲው መስክ የተገኘውን ስኬት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ሀገራቱ የደረሱት ስምምነት አብረው በማደግና ከድህነት ለመላቀቅ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ስምምነቱ ትብብርን፣ የኢኮኖሚ እድገትንና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል በድሬዳዋ እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶች እና በቴክኖሎጂ የታገዙ አገልግሎቶች አሰጣጦች የኢትዮጵያን ከፍታ ጅማሮ አመለካች መሆናቸውን ነው ኃላፊው የገለጹት።

አመራሮች ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና የልማት ጉዞዎችን ለማስቀጠል የተቀመጠውን ሀገራዊ ግብ ለማሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም