በተመድ የደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የታንቡራ ካምፕን አድዋ ካምፕ በሚል ሰየመ - ኢዜአ አማርኛ
በተመድ የደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የታንቡራ ካምፕን አድዋ ካምፕ በሚል ሰየመ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ በተባበሩት መንግስታት የደቡብ ሱዳን ሰላም ማስከበር ሃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ምሃን ሰበርማኒያን የ19ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ የግዳጅ ቀጠና የሆነውንና ቀደም ሲል ታንቡራ ካምፕ በመባል የሚታወቀውን አድዋ ካምፕ በሚል ስያሜ እንዲጠራ ወስነዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ጠንካራና የተሰጠውን ተልዕኮ በላቀ ብቃት እየተወጣ የሚገኝ መሆኑንም ሌተናል ጄኔራል ምሃን ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በደቡብ ሱዳን ለታምቡራ ሰላምና መረጋጋት እያበረከተ ለሚገኘው ሁለንተናዊ ድጋፍ ካምፑ አድዋ በሚል ስያሜ እንዲጠራ መወሰኑን መግለጻቸውን የመከላከያ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ግዳጁን በላቀ ብቃት የሚወጣና ስኬታማ መሆኑን የገለጹት የሃይል አዛዡ በተሰማራበት አስቸጋሪ የግዳጅ ቀጠና ዳግማዊ አድዋ ድል በማስመዝገብ ላይ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የ19ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ አዛዥ ኮሎኔል አለሙ ኪንኪና በበኩላቸው አድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነትና የፅናት ተምሳሌት መሆኑን አብራርተው ካምፑ በአድዋ ስያሜ መጠራቱ የሰራዊቱ የስራ ውጤት በመሆኑ ያስደስታል ብለዋል።
ይህ አይነቱ ሀገርን የሚያስጠራ ስያሜ ማግኘት የሚያኮራ ተግባር መሆኑን ገልጸው ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሃይል ግዳጁን በላቀ ብቃት በመወጣት የኢትዮጵያውያን ኩራት መሆን እንደቻለ ሁሉ ወደፊትም ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡