የአንካራው ስምምነት የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የአንካራው ስምምነት የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ የአንካራው ስምምነት እንደ ሀገር የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰውን የአንካራ ስምምነትን ተከትሎ በሀረሪ ክልል ከአመራሩ ጋር ውይይት ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ እንደገለፁት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰው የአንካራው ስምምነት የጀመርነውን የብልፅግና ጉዞ አንድ ደረጃ ከፍ ያደረገ ነው።
120 ሚሊዮን ህዝብ ያላትን ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር ማሰብ ከባድ ነው ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ አጀንዳ በማድረግ ጥያቄውን እንዴት እንመልስ ወደሚለው ማሸጋገር መቻሉን ገልፀዋል።
የአንካራው ስምምነት ከጦርነት እና ብጥብጥ ይልቅ ሀገራችንን ወደ ዘላቂ ሰላም የሚወስድ ብሎም ወንድማማችነትን የሚያጎለብት ትልቅ ሀገራዊ ድል መሆኑንም ጠቁመዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን ልማት እና ብልፅግና የማይፈልጉ ባገኙት አጋጣሚ ሀገራችንን ወደ ጦርነት አውድማ ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶችን አንገት ያስደፋ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፅዕኖ ለማሳጣት በጎረቤት ሀገራት በጠላትነት ለማስፈረጅ የጠነሰሱትን ሴራ ባዶ ያስቀረ ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለዘመናት የቆየ መሆኑን ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ በታሪክ አጋጣሚ በተሰራው ስህተት ያጣነውን የባህር በር ማስመለስ የአሀኑ ትውልድ ሀላፊነት ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ለቀጣይ የባህር በር ጥያቄ መንገድ የጠረገ ነው የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት ሳንነካ በትውልድ ቅብብሎሽ የበሀር በር ጥያቄያችንን ለማሳካት እንሰራለን ነው ያሉት።
በመሆኑም የባህር በር ጥያቄው ታሪካዊ እና ህጋዊ መሆኑን በመገንዘብ ሀገራዊ እና የአስተሳሰብ አንድነት መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
መንግስት ለሰላም አማራጭ ምንግዜም ክፍት ነው ይህንን ተከተሎም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየተሰራ ነው።
በተለይ በሽግግር ፍትህ የተጀመሩ ስራዎች እንዲሳኩ ሁለም የበኩሉን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ መሳሰባቸውም ተጠቁሟል።
የክልሉ መንግስት ከባህር በር ጥያቄው ጎን ለጎን በተጀመሩ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው የአንካራው ስምምነት ለሀገራችን ዲፕሎማሲ ውጤት እና ያቀድነውን መተግበር እንደምንችል ያረጋገጥንበት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያን መበጥበጥ ሲመኙ የነበሩ ታሪካዊ ጠላቶችን ምቾት የነሳ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
በመደመር መንገድ የማናሳካው ብልፅግና አይኖርም ያሉት አቶ ጌቱ ወዬሳ በቀጣይ እንደ ሀገር ያስቀምናቸውን ግቦች ለማሳካት ሰላማችንን ጠብቀን ሁላችንም በተመደብንበት የስራ መደብ ሀላፊነታችንን መወጣት ይገባል ነው ያሉት።
በአንካራው ስምምነት የተመዘገበውን ድል በተጀመሩ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች አጠናክሮ ለማስቀጠል ርብርብ ይደረጋልምም ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።