ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕን ለመተግበር ያሳየችው ቁርጠኝነት እና ለተግባራዊነቱ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው - ፖል ሲሞን ሃንዲ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህን ለመተግበር ያሳየችው ቁርጠኝነት እና ለተግባራዊነቱ እያከናወነቻቸው ያሉ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሃንዲ ገለጹ።

የሽግግር ፍትሕ ለተጎጂዎች እውቅና ለመስጠት፣ የህዝብ አመኔታን ለማሳደግ፣ የሰብዓዊ መብት መከበርን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና በሕዝቦች መካከል እርቅን ለመፍጠር የሚያስችል ነው።

ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅና ካሳን ያካተተ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ባለፈው ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።

ፖሊሲውን ለመተግበር ህግጋትን ማውጣትን ጨምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሃንዲ ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትሕ ተፈጻሚነት ቁርጠኝነቷን አሳይታለች ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አፅድቃ ወደ ተግባር መግባት የሚያስችሉ ረቂቅ ህጎች ማዘጋጀቷ አስደናቂ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ በሀገር የፍትሕና ዘላቂ ሰላም ግንባታ ላይ ትልቅ መሰረት የሚጥል እና ተስፋ ሰጭ ሂደት መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ረቂቅ ህጎችን ለህዝብ ውይይት መክፈቱ ከዚህ ቀደም ብዙ ያልተለመደና በጎ ትምህርት የሚወሰድበት ነው ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ላይ ሙያዊ ድጋፍ በመስጠት ኢንስቲትዩቱ ማገዙንም አንስተዋል።

በቀጣይ ወደ ትግበራ ሲገባም ከመንግሥት ጋር በቴክኒካዊና ሙያዊ ትብብር እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማስተግበሪያ አዋጆች በሦስት ወራት ጸድቀው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የፍትሕ ሚኒስትሯ ሀና አርዓያ ሥላሴ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ መግለጻቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም