የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ የአፍሪካውያንን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እሰራለሁ - ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ የአፍሪካውያንን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እሰራለሁ - ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ የአፍሪካውያንን ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እሰራለሁ - ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ አስታወቁ።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እጩዎች ክርክር እንደቀጠለ ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ያለውን ክርክር በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ይገኛል።
ክርክሩን እያደረጉ የሚገኙት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ናቸው።
የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥና እድገት በማስመዝገብ ላይ የምትገኝ አህጉር መሆኗን ገልጸዋል።
ይሁንና የአፍሪካ ሀገራት ለልማት እና እድገት ስራዎቻቸው በሚፈለገው መጠን ፋይናንስ እያገኙ አለመሆኑን አመልክተዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ ሁሉን አካታች የሆነ የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሁሉም አፍሪካዊ ሰርቶ የመለወጥ እና የማደግ መብት አለው ያሉት ራንድሪያማንድራቶ ዜጎች የስራ እድል አግኝተው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ከዋነኛ ስራዎቻቸው መካከል አንዱ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
የአፍሪካንና የሀገራትን ጥቅል ዓመታዊ የኢኮኖሚ እድገት የሚያሳድጉ የማሻሻያ ስራዎችን እንደሚያከናውኑም አመልክተዋል።
አፍሪካ በፍጥነት እየተለወጠች እና እያደገች ቢሆንም የአህጉሪቱ ዋና ተቋም የሆነው የአፍሪካ ሕብረት በሚፈለገው መጠን አቅሙ አለማደጉን ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ በአፍሪካ ሕብረት ላይ ተቋማዊ ማሻሻያ በማድረግ ተወዳዳሪነቱን ለመጨመር እና የውሳኔ ሰጪነት አቅሙን ለማጠናከር እንደሚሰሩ አመልክተዋል።