ቀጥታ፡

ባህላዊ ሽምግልና እና የዕርቅ ስርዓትን በማጠናከር የፍርድ ቤቶችን ጫና ማቃለል ይገባል - አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

ባህር ዳር፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ ባህላዊ ሽምግልና እና የዕርቅ ስርዓትን በማጠናከር የፍርድ ቤቶችን ጫና ማቃለል እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ አስገነዘቡ።

በባህላዊ የዕርቅ ስርዓት፤ በፍርድ ቤት መር አስማሚነትና በግልግል ዳኝነት ላይ አተኩሮ የተዘጋጀ አውደ ጥናት በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ የፍትህ ተቋማት አመኔታን ለማረጋገጥ በፍርድ ቤት ብቻ ሁሉንም ተደራሽ ማድረግ አይቻልም።

ህብረተሰቡ ያለውን ማህበራዊ ትስስር አጠናክሮ ለማስቀጠል ባህላዊ የሽምግልናና የዕርቅ ስርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።

ባህላዊ የዕርቅ ስርዓቶች ዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ባልተቋቋሙበት ዘመን ሲሰራባቸው የቆዩና አሁንም እየተሰራባቸው የሚገኙ ናቸው ብለዋል።

እነዚህን መልካም ተግባራት የበለጠ በማጎልበት የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታትና የፍርድ ቤቶችን ጫና ለማቃለል ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።


 

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በፍትህና በዳኝነት ዘርፉ የተለያዩ የለውጥ ስራዎች መተግበራቸው አወንታዊ ውጤት መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርምያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) ናቸው።

በተደረጉ በርካታ የህግ ማሻሻያዎችም አፋኝ፣ ጨቋኝና አግላይ የነበሩ ህጎችን በማሻሻል በፍትህ ስርዓቱ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉን አመልክተዋል።

ለረጅም ዘመናት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘውን ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን በህግ ዕውቅና ሰጥቶ መጠቀም የፍርድ ቤቶችን ጫና በመቀነስ ቀልጣፋና ወጭ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት የጎላ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።


 

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት፤ የዳኝነትና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ በተለያየ ጊዜ የፍትህ ማሻሻያ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ለዚህም በፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተካተቱ አምዶች አንዱ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም መደበኛውን የፍትህ ስርዓት ጫና በመቀነስ የዳኝነትና የፍትህ ስርዓቱ ቀልጣፋና ውጤታማ በማድረግ የተገልጋዩን ህብረተሰብ እርካታ ለማሳደግ ድርሻቸው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።

ባህላዊ አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች የዳኝነትና የፍትህ አገልግሎቱን ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ ዕውነትን ለማውጣት፣ ቁርሾና በደሎች እንዲሽሩ ለማድረግ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

ባህላዊ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች አገልግሎት የሚሰጡ አካላትም በቂ ዕውቀትና ልምድ እንዲኖራቸው በማስቻል መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ አግባብ መተግበር ይኖርባቸዋል።

ክልሉ የቆየና የዳበረ የግጭት አፈታት ስርዓትና ባህል ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው፤ ተጨማሪ ተሞክሮዎችን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም ላይ ለማዋል መድረኩ መዘጋጀቱን አስገንዝብዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ አውደ ጥናት የሌሎች ክልሎች ባህላዊ የዕርቅ መፍቻ ስርዓቶች ልምድና ተሞክሮ እንዲሁም የዘርፉ ምሁራን ጥናቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም