ራይላ ኦዲንጋ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ የአፍሪካ አንድነትን ማጠናከር ዋነኛ የትኩረት ማጠንጠኛቸው እንደሚሆን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ራይላ ኦዲንጋ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ የአፍሪካ አንድነትን ማጠናከር ዋነኛ የትኩረት ማጠንጠኛቸው እንደሚሆን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሆነው ቢመረጡ የሕብረቱ መስራች አባቶች ሕልም የሆነውን አፍሪካን አንድ የማድረግ ውጥን ማሳካት ዋነኛ ትኩረታቸው እንደሚሆን የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ ገለጹ።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ምርጫ እጩዎች ክርክር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ያለውን ክርክሩን በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈው ይገኛል።
ክርክሩን እያደረጉ የሚገኙት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ናቸው።
የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የአፍሪካ ሕብረት (በቀድሞ መጠሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) ከተመሰረተ 61 ዓመታት ማስቆጠሩን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት መስራች አባቶች ሁሌም ስለ አህጉሪቱ አንድነት አጥብቀው ይናገሩ እንደነበርና አሁንም በአጀንዳ 2063 አንድነቷን እውን ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የአፍሪካን አንድነት ለማረጋገጥ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ እንደነበራቸው የገለጹት ኦዲንጋ አህጉሪቱ ከቅኝ ገዢዎች እጅ ብትላቀቅም አሁንም ብዙ ስራ እንደሚጠብቃት ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በመሆን ቢመረጡ ባላቸው ልምድ የአፍሪካን አንድነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።
በትምህርት፣ በጤና፣ በምርቶች እሴት መጨመር እና በተለያዩ ቁልፍ መስኮች ላይ በትኩረት እሰራለሁ ብለዋል።
በተለይም የአፍሪካን ይእርስ በእርስ የንግድ ምጣኔ ለማሳደግ እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች የማስፋፋት እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ የአፍሪካ ሕብረት መስራች አባቶችን ሕልም እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እሰራለሁ ሲሉ ተናግረዋል።