ቀጥታ፡

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እሰራለሁ - መሐሙድ አሊ የሱፍ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው ቢመረጡ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ ገለጹ።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እጩዎች ክርክር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ያለውን ክርክሩን በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ይገኛል።

ክርክሩን እያደረጉ የሚገኙት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ናቸው።

የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ አፍሪካ በሰላምና ደህንነት፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ልማት እና በኢኮኖሚ ትስስር በሚፈለገው ፍጥነት እየሄደ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ይሁንና በአጀንዳ 2063 በተያዘው የምንፈልጋት አፍሪካ ትልም እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ለውጦች እየታዩ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው ቢመረጡ በሰላም እና ደህንነት በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ተጠባባቂ ወታደራዊ ኃይል ወደ ስራ እንደሚገባ እና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ፈንድ አማካኝነት የአህጉሪቷን የሰላምና ደህንነት አጠናክራለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

በአፍሪካ አደጋዎችን ለመከከል የአባል አገራትን የቅድመ አደጋ መቆጣጠር ስርዓት እንዲጠናከር እንደሚያደርጉም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕዝብ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘውን ወጣት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችንም እንደሚተግብሩ ጠቁመዋል።

በአፍሪካውያን መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲጎለብት እና ነጻ የሰዎች እንቅስቃሴ እንዲኖር በትኩረት እንደሚሰሩም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ፣ አገልግሎት እና የተለያዩ ዘርፎች እድገትን ለማሳላጥ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንደሚወስዱም አመለክተዋል።

የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሆኜ ብመረጥ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እሰራለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም