በትግራይ ክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የልማት ፕሮጀክቶችን በተጠናከረ መልኩ እንዲሰሩ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የልማት ፕሮጀክቶችን በተጠናከረ መልኩ እንዲሰሩ ተጠየቀ
መቀሌ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ላይ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ባለስልጣን ጠይቋል።
ኬር ኢትዮጵያ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን በግብርና፣ በጤና እና በንፁህ መጠጥ ውሃ ዘርፎች ያከናወናቸው የልማት ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለፁት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህዝብን ጥቅም ለማረጋገጥ የጀመሯቸውን መልካም ተግባራት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው።
ድርጅቶቹ ሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በዘላቂነት የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ከዚህ አኳያ ኬር ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል እያከናወናቸው ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ መሆናቸውን መገንዘባቸውን አቶ ፋሲካው አስረድተዋል።
በገጠር የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ኬር ኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ገብረሚካኤል ገብረክርስቶስ ናቸው።
የኬር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ቶማስ ዋይት በበኩላቸው፤ በተለያዩ ክልሎች በግብርናና ገጠር ልማት እንዲሁም በጤና ዘርፍ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን በአራት ወረዳዎች ላይ ሰባት በጸሃይ ሃይል የሚሰሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለአገልግሎት ማብቃታቸውን ተናግረዋል።
ከመንግስትና ማህበረሰብ ጋር በመተባበርም ችግር ፈቺና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ ምስራቃዊ ዞን የፋፂ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አዝመራ ገብረክርስቶስ በታዳሽ ሃይል የሚሰራው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑ ገልፀዋል።
በዞኑ ጉሎመኸዳ የመስተፍቃዳ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃነ ገብረ ፃድቃን በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ባደረገላቸው የእርሻ መሳሪያዎች እና የምርጥ ዘር ድጋፍ አምርተው ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል።