የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እጩዎች ክርክር እያካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እጩዎች ክርክር እያካሄዱ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እጩዎች ክርክር እያካሄዱ ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሕብረቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ያለውን ክርክር በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፈ ይገኛል።
ክርክሩን እያደረጉ የሚገኙት የጅቡቲ የውጭ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሐሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና የማዳጋስካር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪቻርድ ራንድሪያማንድራቶ ናቸው።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ከምስራቅ አፍሪካ ቀጣና እንደሚመረጥ ይታወቃል።
የሊቀመንበርነት ምርጫው የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ይከናወናል።
ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ምርጫ ውጪ በዘንድሮው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚሚሽኑ ምክትል ሊቀ መንበር እንዲሁም በኮሚሽኑ ስር ያሉ የስድስት ኮሚሽነሮች ምርጫ ይካሄዳል።
የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ“ እና ዘላቂ ከባቢ አየር የኢኮኖሚ ልማት፣ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ማዕድን፤ የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ፣ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደህንነት፤ የጤና፣ ሰብአዊ ጉዳዮችና ማህበራዊ ልማት፤ ስድስቱ የኮሚሽነሮች ምርጫ የሚካሄድባቸው የስልጣን ቦታዎች ናቸው።
ከእ.አ.አ 2017 አንስቶ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የ64 ዓመቱ የቻድ ፖለቲከኛ እና ዲፕሎማት ሙሳ ፋቂ ማህማት የስልጣን ጊዜያቸው በቅርቡ ይጠናቀቃል።