የምስራቅ አፍሪካ የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ ጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ ጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የህጻናት ጉዳይ የሚመለከታቸው ሚኒስትሮች የቀጣናውን የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፍ አጸደቁ፡፡
የፖሊሲ ማዕቀፉ በኢጋድ ቀጣና የሚኖሩ ህጻናት የሚያጋጥማቸውን ችግር በመፍታት ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ የአሰራር ማዕቀፎችን የሚዘረጋ ነው ተብሏል።
ፖሊሲው በቀጣናው በህጻናት ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ፍትህ፣ የህጻናት ተሳትፎ ማሳደግን ጨምሮ 10 ቁልፍ ጉዳዮችን አካቷል።
በህጻናት ላይ የሚደረግ መገለል፣ የጉልበት ብዝበዛና ሌሎች በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ የሚደረጉ እቅዶችንም የያዘ መሆኑም ተመላክቷል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የጤና እና ማህበራዊ ልማት ዘርፍ ዳይሬክተር ፈትያ አሉዋን ኢጋድ ለሰላም፣ ማህበራዊ ደህንነትና ምጣኔ ሃብት እድገት ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።
ለእነዚህ ጉዳዮች መሳካት የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ህጻናት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ለዚሁ ስኬት የፖሊሲ ማዕቀፉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት ፖሊሲው በአባል ሀገራት መካከል ትብብርን በማጠናከር የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ ያግዛል።
በቀጣናው የሚኖሩ ህጻናት ለድህነት፣ ለግጭት እንዲሁም በትምህርት ተደራሽ አለመሆንን ጨምሮ ለሌሎች ችግሮች ተጋላጭ መሆናቸውን በመጥቀስ ችግሩን ለመቅረፍ ትብብርን በማጠናከር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ በ2017 ተግባራዊ ባደረገችው የህጻናት ፖሊሲ ከቀበሌ ጀምሮ የህጻናትን ደህንነት ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ዘርዝረዋል።
የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋትና የትምህርት ቤት ምገባን በመጀመር ህጻናት በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የሚረዱ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የህጻናት ፖሊሲ ማዕቀፉን ከብሔራዊ ፖሊሲዋ ጋር በማቀናጀት ከአባል ሀገራቱ ጋር በትብብር ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የደቡብ ሱዳን የስርአተ-ጾታ፣ ህጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አያ ቤንጃሚን ሊቦ(ዶ/ር) እና የኡጋንዳ የህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ባላም አቲንይ(ዶ/ር) ለቀጣናዊ ችግር መፍትሄ ለማምጣት ትብብርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በኬንያ ሰራተኛና ማህበራዊ ጥበቃ ሚኒስቴር የህጻናት አገልግሎት ዳይሬክተር አዋምቢ ሞንጋሪ እና የሶማሊያ የቤተሰብና ሰብአዊ መብት ልማት ሚኒስትር ተወካይ በበኩላቸው የፖሊሲ ማዕቀፉ የያዛቸውን ግቦች ለማሳካት ቀጣናዊ ትብብርን በማጠናከር ለመስራት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች የአባል አገራቱ ተወካዮችና አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለፖሊሲ ማዕቀፉ ተግባራዊነት በትብበር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።