ቀጥታ፡

ሰላም ሚኒስቴር እና ዩኒሴፍ በግጭት መከላከል እና በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ ሰላም ሚኒስቴር እና የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) በግጭት መከላከል እና በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ(ዶ/ር) ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡


 

በውይይታቸውም ሚኒስትሩ ዘላቂ ሰላም ከመገንባት፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ከመመለስ፣ ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ከመስጠት እና ብሔራዊ መግባባትን ከመፍጠር አንጻር ሚኒስቴሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አብራርተዋል፡፡

የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አቡበከር ካምፖ(ዶ/ር) በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር ዘላቂ ሰላም ከመገንባት አኳያ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ከተቋማቸው ተልዕኮ ጋር የሚናበብ መሆኑን መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም ሁለቱ ተቋማት በግጭት መከላከል እና በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም