ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የነበሩበትን ችግሮች በመሻገር በፕሮጀክት አፈጻጸም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የነበሩበትን ችግሮች በመሻገር በፕሮጀክት አፈጻጸም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮርፖሬሽኑን የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን እና የልህቀት ማዕከልን ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የማንሠራራት ዘመን ከሚያበስሩ ሞዴል ተቋማት አንዱ ወደ መሆን መሸጋገሩን አንስተዋል።

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ትርፋማና ውጤታማ እንዲሆኑ በተሰጠው የሪፎርም ትኩረት ኮርፖሬሽኑ ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች መውጣቱን ተናግረዋል።

ምቹ የሥራ ከባቢን በመፍጠር ምርታማ የሥራ ሂደትን እየተከተለ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት በጥሩ መሠረት ላይ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ በውጭ ሀገራት ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ የጀመረውን ሥራ ማፋጠን አለበት ብለዋል።

መንግሥትም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ።

በፕሮጀክት ግንባታ፣ በግብዓት ማምረቻ፣ በኢንዱስትሪ እና በዲጂታላይዜሽን ዘርፎች የጀመራቸው ተግባራት ከተልዕኮው ጋር የተናበቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ ባካሄደው ሪፎርም ችግሮቹን በመሻገር በፕሮጀክት አፈጻጸም ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪም ጉልህ ሚና የሚጫወት መሆኑን በመጥቀስ ትርፋማነቱን ማሳደግ እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ ለሌሎች አርዓያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው፤ ኮርፖሬሽኑ አሠራሩን የማዘመን እንዲሁም በፕሮጀክት ማኔጅመንትና ዲጂታላይዜሽን ሪፎርሞችን ማካሄዱን ተናግረዋል።

ብቁ ሙያተኞችን በመፍጠርና በቴክኖሎጂ ልህቀት ዓለም የደረሰበትን የኮንስራክሽን አቅም መፍጠሩንም አንስተዋል።

በዚህም ተገጣጣሚ ህንፃ እና ሌሎች የግንባታ ግብዓቶችን በፍጥነት እያመረተ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግሥት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት እንዲያቀርብ ትልቅ አቅም መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ ዓመታት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሽን ኢንቨስተር የመሆን ግብ ይዞ እየሠራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዞንና የልህቀት ማዕከል የተገጣጣሚ ህንጻ፣ የጎማ መልሶ መጠቀሚያ፣ የፕላስቲክ ፓይፕ፣ አልሙኒየም፣ እንጨት፣ ብረታ ብረት፣ የትራፊክ መብራት፣ ብሎኬት፣ የአሽዋ ውህድ እና ሌሎች ምርቶችን በማምረት ላይ ይገኛል።

የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ጥገና፣ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ስልጠና በመስጠት ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ከማብቃት አንጻር የልህቀት ማዕከል ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም