በደሴ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የልማት ተግባራት እንዲጠናከሩ ድጋፍ ይደረጋል - የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

ደሴ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ድጋፍ እንደሚደረግ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በደሴ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ በደሴ ከተማ እየተካሄዱ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አበረታች ናቸው።


 

በከተማ አስተዳደሩ እየተከናወኑ ካሉና ከተመለከቷቸው አበረታች ተግባራት መካከል የኮሪደር ልማት፤ ስማርት ሲቲ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥና የሌማት ትሩፋትን ጠቅሰዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማቱ ደሴን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ በኢትዮጵያ ካሉ አቻ ከተሞች ጋር መወዳደርና እኩል ማደግ እንድትችል መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለከተማው ሁለንተናዊ ልማትና እድገት የፌዴራል መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡


 

ህብረተሰቡም የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ በከተማው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላሙን ከመጠበቅ ባለፈ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡


 

በተለይ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት ማምጣቱን ጠቁመው፤ በኮሪደር ልማት፣ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ዘርፎች የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የደሴ ኮሪደር ልማት፣ የሌማት ትሩፋት፣ ስማርት ሲቲና ሌሎችንም የልማት ስራዎች ተመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም