ስማርት ከተማን ከመገንባት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካል ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ስማርት ከተማን ከመገንባት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካል ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ስማርት ከተማን ከመገንባት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካል ንቁ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለፀ።
የአዲስ አበባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ “የሳይበር ደህንነት ለስማርት ሲቲ” በሚል መሪ ሃሳብ ሲምፖዚየም አካሂዷል።
በዚህ ወቅት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ እንዳሉት አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ፣ አዲስና ለነዋሪዎቿ ተስማሚ “ስማርት ከተማ” ለማድረግ አበረታች ስራ እየተከናወነ ነው፡፡
ከተማዋ ወደ ስማርት ሲቲ እያደረገች ባለው ጉዞ ለሳይበር ጥቃቶች እንዳትጋለጥ የከተማዋን የሳይበር ደህንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ስማርት ከተማን ከመገንባት ባለፈ ደህንነቱ የተጠበቀ የሳይበር ምህዳር ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ሊያደረጉ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም የዜጎችን የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማሳደግና የሳይበር ስጋት መረጃ መለዋወጥ ላይ በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በሳይበር ደህንነት ዙሪያ መድረክ ማዘጋጀቱ በዘርፉ ግንዛቤን ለማሳደግ ከማስቻሉ በተጨማሪ ለከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገትና ብልጽግና አስቻይ መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሰለሞን አማረ በበኩላቸው በከተማው ስማርት ሲቲ ትግበራ ላይ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባን በምስራቅ አፍሪካ በሳይበር ደህንነት የተሻለች ከተማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ቢሮው ከ2015 እስከ 2023 ዓ.ም የሚተገበርና ከተማዋን የቴክኖሎጂ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል የስማርት ሲቲ ስትራቴጂ አዘጋጅቶ ወደ ስራ ማስገባቱንም ጠቅሰዋል።
ይህንኑ ተከትሎ በከተማዋ እስከ ወረዳ ያሉ ቢሮዎች በ"ሲቲ ኔት" ኔትወርክ መተሳሰራቸውን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
ለዚህም የአሰራር ስርዓት፣ የቴክኖሎጂ ትግበራና የሰው ኃይል ማብቃት ላይ እየተሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት የሰው ኃይሉን ለማብቃት በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ሲሰጡ መቆየቱን በአብነት አንስተዋል።
በስማርት ሲቲ የሚሰሩ የዲጂታል መሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂዎችን ለመጠበቅ የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ስልጠና ዲጂታል ሰራዊትን ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡